አሜሪካ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩትን እንቅስቃሴ እደግፋለሁ አለች

83
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 አሜሪካ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2010 ዓ.ም በኤርትራ አስመራ ባደረጉት ጉብኝት ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አገራቱ ያለባቸውን አለመግባባት ወደ ጎን በማድረግ ግንኙነታቸውን ማጎልበት በሚችሉበት ላይ ተወያይተዋል። አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በድጋሚ ለመጀመር በኢኮኖሚና ሌሎች መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውና መሪዎቹ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል። አሜሪካም የሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት ለሰላምና ለደህንነት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሚያሳይና ይህንንም እንደምታደንቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖምፒዮ በኩል ገልጻለች። የሁለቱ አገራት ስምምነት ለ20 ዓመት የቆየውን ጦርነት በይፋ እንዲቆም ያደረገ እንደሆነም አስታውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዜጎቻቸውን ወደ ሰላም፣ ብልጽግናና ፖለቲካዊ ማሻሻያ የሚመራ ብርታት የተሞላበት ቁርጠኝነታቸው ምስጋናዋን አቅርባለች። ሁለቱ አገራት ግንኙነት መጀመራቸውና የተፈራረሙት የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት የአገራቱ ዜጎች የጋራ ህልም  በሆነው የኢኮኖሚ፣ ፖሊቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የቀረበ ትስስር እንዲያተኩሩ መልካም እድልን እንደሚፈጥርም ተገልጿል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩትን ሂደት አሜሪካ ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነች ገልጻ፤ ሁሉም አካላት በቀጣይ ጊዜያት በግልጽነትና በመተማመን እንዲሰሩ ጠይቃለች። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም መኖር ለአፍሪካ ቀንድና ለቀይ ባህር መረጋጋት፣ ሰላም፣ ደህንነትና ልማት መሰረት እንደሚሆን ነው የአሜሪካ መንግስት ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም