የሕዳሴውን ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዳጠናቀቅን ሁሉ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በጋራ እንግታ - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴውን ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዳጠናቀቅን ሁሉ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በጋራ እንግታ - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዳጠናቀቅን ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በጋራ እንግታ ሲል ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
ሚኒስቴሩ "ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ መላ ኢትዮጵያዊያንን በንቃት ያሳተፈ፣ የአገራችንን የብልጽግና ተስፋ አስቀድሞ የፈነጠቀና ብርሃን ያሳየ፤ የይቻላል መንፈስንም በተግባር ያመላከተ የአንድነታችን ምሰሶ ነው" ብሏል።
የጤና ሚኒስቴር በዓለም እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሕዝቡ ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የጋራ ርብርብ እያደረግን ባለንበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሕዳሴ ግድባችን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የሚነስቴሩን የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በእጅጉ አስደስቶናል ብሏል።
"እኛ ኢትዮጵያዊያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያሳየነው አንድነትና ያልተቋረጠ ተሳትፎ ግድቡን ወደዚህ የከፍታ ምዕራፍ አድርሶታል" ያለው ሚኒስቴሩ ሕዝቡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሚደረገው ርብርብም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉን ለአፍታም ሳይዘነጋ የመከላከያ መንገዶችን እንዲተገብር አሳስቧል።
የሕዳሴ ግድባችን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መሳካቱ የአገራችንን የብልጽግና ጉዞ አይቀሬነት በግልጽ ያመላከተ ሲሆን እኛ ኢትዮጵያዊያንም የስኬቱን የመጨረሻ ውጤት የምናጣጥመው የራሳችንን፣ የቤተሰባችንንና የማኅበረሰባችንን ጤና በግልና በጋራ ጥረት ስንጠብቅ ነው ብሏል።
"ሁላችንም ርቀታችንን በመጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ ማስክ በመጠቀም፣ አስገዳጅ ካልሆነ በቀር ከቤታችን ባለመውጣት፣ እጃችንን በሳሙናና በውሃ በመታጠብ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሳየነውን ተሳትፎና ያመጣነውን ድል በኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር እንደምንደግመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጽኑ ዕምነት አለው" ይላል የሚኒስቴሩ መግለጫ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎችና በዚህም ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም በአጽንኦት አሳስቧል።