ቀጥታ፡

የንግዱ ማኀበረሰብ ከግድቡ ፍሬ ተቋዳሽ አጋርነቱን ማሳየት ይኖርበታል- ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012( ኢዜአ) የንግዱ ማኀበረሰብ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍሬ ተቋዳሽ ለመሆን የሚቆጥበው እውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ሳይኖር አጋርነቱን ማሳየት ይኖርበታል ሲል የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። ማህበረሰቡ ለህዳሴ ግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጿል።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ አውጥቷል።

የህዳሴ ግድቡ የኢኮኖሚ እድገት ማማ መውጫ መሰላላችን ነው፤በአገሪቷ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት፣የስራ ዕድልን በመፍጠር፣የውጭ ምንዛሬን ፍላጎት በሟማላት በኩል ትልቅ ድርሻ እንዳለው ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።    

ግድቡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው ያለው ምክር ቤቱ፤ ግድቡ የመኖር ወይም ያለመኖር ዋስትናችንም ጭምር ነው ብሏል።  

በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የቦንድ ግዥ በመፈጸምና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ አካሄዱ እያማረ ያለውን ግድብ እጅ ለእጅ ተያይዘን እስከ መጨረሻው እናሳካ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ከግድቡ ፍሬ ተቋዳሽ ለመሆን የምንቆጥበው እውቀት ጉልበት፣ገንዘብ ሳይኖር አጋርነታችንን ማሳየት ይኖርብናል ሲል ነው ምክር ቤቱ መልዕክት ያስተላለፈው።   

ዓባይ የሰላማችን የአንድነታችን መሰረት መሆኑን ያመለከተው መግለጫው አባይ አንድ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚያችን ጋር የተሳሰረ የእድገት መውጫችንም ጭምር መሆኑን ተደጋግሞ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑም ምክር ቤቱ ያምናል ብሏል።

እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር የሚመጥን የውሃ ኤሌክትሪክና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን መመለስ ካልተቻ አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ግድቡን ለአገልግሎት ማብቃት ወሳኝ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጠው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም