የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ በመከናወኑ የተለያዩ አካላት ደስታቸውን እየገለጹ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ በመከናወኑ የተለያዩ አካላት ደስታቸውን እየገለጹ ነው
አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ በመከናወኑ የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
ለኢዜአ የደስታ መልዕክት ከላኩ ተቋማት መካከል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌት በመጠናቀቁ የተሰማውን ደስታ ገልጾ ለህዝቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የነገውን የአገራችንን ተሰፋ ያለመለመ ብቻ ሳይሆን ለተጨማሪ ድሎች የሚያነሳሳ ነው ሲልም ገልጿል፡፡
በቀጣይም ግድቡን በመጠበቅ መሰረታዊ ዓለም አቀፍ ህግጋትን በማክበር የተፈጥሮ ፀጋችንን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ የመጠቀም መብታችንን ሳንደራደር የሚቀጠል መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም እንዲሁ የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ ደስታ እንደተሰማው ገልጿ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በበኩሉ የግድቡን ሙሌት አስመልክቶ ባስተላለፈው የደስታ መግለጫ የዓባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ሃብቷን ሳትጠቀም በርካታ ዘመናት እንዳለፉና ጎረቤት አገራት ከአባይ ጸጋ ራሳቸውን ሲያበልጽጉ እንደኖሩ ገልጿል።
የውሃ ሙሌቱ ይሄን አስገራሚ እንቆልሽ የፈታ በመሆኑ የተሰማን ደስታ ወሰን የለውም ነው ያለው ፓርቲው። ለሁሉም ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች ደስታችንን ለመግለፅ እንወዳለን ሲልም አክሏል በመግለጫው።
የግድባችን ውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መቀላጠፉ ደስታና እርካታ ነው ያለው ትዴፓ የህዳሴው ግድብ የመጨረሻው ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን መንግስት ከትናንት በስቲያ መግለጹ የሚታወስ ነው። ለመጀመሪያው ዙር የሚያስፈልገው የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙንም አመልክቷል።