በአማራ ክልል ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰብል ዘር ተሸፈነ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰብል ዘር ተሸፈነ
ባሀርዳር ሐምሌ 15/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰብል ዘር መሸፈን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በዘር የተሸፈነው መሬት በምርት ዘመኑ ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ ነው።
በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የእርሻ መሬቱ የተሸፈነው በበቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ቢራ ገብስ፣ ሰሊጥና ሌሎች ሰብሎች ነው።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም ግማሽ ያህሉ በመስመር የተዘራ መሆኑን አመልክተዋል።
የእርሻና የዘር ስራው የተከናወነውም የግብርና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተሻሻሉ አሰራሮችና ግብዓትን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም እየተደረገ ነው ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም ስድስት ሚሊዮን 400ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያ መቅረቡንና ከዚህም ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጥቅም ላይ መዋሉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በከሮና ቫይረስ ምክንያት የምግብ እጥረት እንዳያገጥም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል 120ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰራጨቱን አስታውቀዋል።
ዘንድሮ ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ቀድሞ በመግባቱም የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በአርሶ አደሩ ዘንድ አለመኖሩን ገልጸዋል።
በመጪው መኸር 127 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በቀጣይ ጊዜያት ቀሪውን መሬት ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች ለመሸፈን አርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የዱርጌማሽንት ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃን ይመር በሰጡት አስተያየት፤ ያላቸውን ሶስት ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ፣ ስንዴ፣ ድንችና ባቄላ የሰብል ዘሮች በመሸፈን እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ባለሙያዎች በሚያደርጉላቸው ድጋፍና ክትትል የማዳበሪያ ግብዓትን ጨምሮ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮ ማዳበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ መሬታቸውን በጊዜው በዘር ለመሸፈን እንዳገዛቸው የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ደንበጫ ወረዳ የእግዚአብሄርአብ ቀበሌ አርሶ አደር አብራራው ፈንቴ ናቸው።
አርሶ አደሩ እንዳሉት የእርሻ ማሳቸውን በበቆሎ፣ ዳጉሳና ስንዴ ዘር ለማልማት ማዳበሪያ ገዝተው ተጠቅመዋል።
የተሻለ ምርት ለማግኘትም ከዘር ስራው በተጓዳኝ እራሳቸውን ከኮሮና በመጠበቅ የኩትኳቶና አረም ስራቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በክልሉ በ2011/2012 የመኽር ወቅት ከለማው መሬት ከ108 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለም ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።