የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ስድስት ተቋማት እንደሚደራጁ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ስድስት ተቋማት እንደሚደራጁ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገዋል።

ዘርፉ 80 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ድርሻ ያየዘ እንደ ሆነ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ አስታውሰው፤ ''ይህ ግዙፍ ዘርፍ የተደራሽነት፣ የፖሊሲ ክፍተት፣ የትብብርና የቅንጅት እንዲሁም የውክልና ችግር አለበት'' ብለዋል።

የህግ አፈጻጸም ክፍተት፣ የሴቶችና ወጣቶች ውክልና ማነስ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የኃይል ጥቃቶች መበራከትንም ጠቅሰዋል።

የዘርፉን ችግር በተቀላጠፈ መልኩ ለመፍታት ስድስት ተቋማት በቀጣዮቹ ዓመታት እንደሚደራጁ ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

ከነዚህ ተቋማት መካከል የህጻናት ማህበራዊ አገልግሎት ኤጀንሲ፣ ሁሉን አቀፍ የህፃናት የገንዘብ ድጋፍና የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል እንደሚኖሩበት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ የሴቶች የአመራር ማዕከል፣ የሴቶች የገበያ ማዕከልና የጸረ ጥቃት ፖሊስ ግብረ ኃይልም እንደሚደራጅ ገልጸዋል።

''እነዚህ ተቋማት ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ'' የሚል እምነት ያላቸው ሚኒስትሯ፤ ''13 ሚሊዮን ህጻናት ከድሃ ቤተሰብ ጋር እንደመኖራቸው እነሱን የሚመለከቱት ተቋማት መኖራቸው ጥቅማቸው የጎላ ነው'' ብለዋል።

ከ'ያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ' ተጋብዘው ዕቅዱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር አሉላ ፓንክረስት ''ህጻናትን በሚመለከቱ ተቋማት ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል'' ብለዋል።

ድህነት ከማንም በላይ ህጻናትን በመግለጽ፤ ትብብር የሚፈልግ በመሆኑ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

''የህጻናት ማህበራዊ አገልግሎት ኤጀንሲ ለማቋቋም መታሰቡ የሚደገፍና የሚበረታታ ዕቅድ ነው'' ብለዋል።

ፕሮፌሰር አሉላ ዓለም ላይ 108 አገሮች የህጻናት ተጠቃሚነት ድጎማ እየተገበሩ መሆኑን እንደምሳሌም አንስተዋል።

''የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል ለመመስረት መታሰቡም የተሻለ ዕቅድ ነው'' ያሉት ደግሞ አቶ ኢሳያስ አለማየሁ ናቸው።

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ፤ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ በርካታ የወጣቶች ማህበራት ቢመሰረቱም ውጤታማነታቸው እምብዛም ነበር።

''የአሁኑ የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል ግን ያለምንም ልዩነት ሁሉንም ወጣት ማሰበሰብ የሚችል ከሆነ ትልቅ ለውጥ ያመጣል'' ብለዋል።

የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ በየዘርፉ ውይይት እየተደረገ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም