ኮሚሽኑ የእስረኛ አያያዝ ላይ ምክረሃሳብ የሰጠባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የእስረኛ አያያዝ ላይ ምክረሃሳብ የሰጠባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው
አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ከተሰከተው ችግር ጋር ተያይዞ በህግ ጥላ ስር ስላሉ እስረኞች አያያዝ ያቀረበው ምክረሃሳብ ተግባራዊ መደረጉን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተውን መጠነ ሰፊ የጸጥታ ችግር፣ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት በሚመለከት ከመነሻው ጀምሮ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምርመራ ስልት ላይ የተመሰረተና በበቂ ማስረጃዎች የተደገፈ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን አይነት በተገቢው መጠን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን አዋቅሬ ወደ ሥራ ገብቻለሁም ብሏል።
እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ቅድመ ጥናት ሰፊ ችግር የተከሰተባቸው ተብለው በተለዩ 15 ቦታዎች ላይ ምርመራው ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚካሄድና በተጨማሪም አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች መጠነኛ ችግር በተከሰተባቸው ወደ 40 የሚሆኑ ቦታዎች ላይም ስለ ደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጠቃላይ መረጃ የሚሰበስብ መሆኑንም ነው የገለፀው።
የምርመራው ውጤት የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓይነት፣ መጠን እና አዝማሚያ ለመለየት፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የተጐዱ ሰዎች የሚካሱበትና መልሶ የሚቋቋሙበት እንዲሁም መሰል ድርጊትን ለመከላከል ስለሚያስችሉ እርምጃዎች ግብዓት እንደሚሆን እንደሚታመን አብራርቷል።
ኮሚሽኑ ስለ አደጋው ሁኔታ መረጃና ማስረጃ ያላቸው ሰዎች ወይም ድርጅቶች ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን እንዲቀጥሉም ነው ጥሪ ያቀረበው።
አደጋውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ያስታወሰው መግለጫው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ ኮሚሽኑ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁሟል።
ቀደም ሲል ታሳሪዎች የሚገኙባቸውን ማረሚያ ቤቶች በመጎብኘትና እስረኛና ሃላፊዎችንም በማነጋገር ጭምር የአያያዝ ሁኔታውን በማድነቅ መስተካከል ስላለባቸው ጉዳዮች ደግሞ ምክረሀሳብ መስጠቱም ይታወሳል።
ኮሚሽኑ የሰጠው ምክረ ሃሳብ በሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተግባራዊ መደረጉን በመግለጽም በመልካም እርምጃነቱ እውቅና ሰጥቷል።
በአብዛኛዎቹ ታሳሪዎች እንደተገለጸለትም ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን መረዳቱንም ገልጿል።
በሌላ በኩል ከታሳሪዎች የቀረቡትን መጠነኛ ቅሬታዎች ሊሻሻሉ ስለሚችሉበት መንገድ ኮሚሽኑ ከኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉንና አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታተል አሳውቋል።