ቀጥታ፡

የሶስትዮሽ ድርድሩ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተገኘበት ነው...የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2012(ኢዜአ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ማዕቀፍ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተገኘበት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ስለተከናወኑ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪው ምዕራፍ የውሃ ሙሌት እና በዜጋ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣ መግለጫ ሰጥተዋል።

የግድቡን ውሃ ሙሌት አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከፈለጉ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ለዓለም ያሳዩበት፤ ትልቅ መልዕክት የፈጠረ ነው።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ሲንከባለል የነበረውን የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ተካሂዶ ቀደም ሲል ከነበሩት በአንጻራዊነት ውጤታማ መሆኑ፤ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ማዕቀፍ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንደሆነ ተናግረው፤ ለዚህም የህብረቱ የወቅቱ የስራ ሃላፊዎችን አመስግነዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ተግባር መከናወኑን ገልጸው፤ በኮቪድ-19 ምክንያት ስራዎቹ የተካሄዱት በዌቢናር ወይም በቨርቹዋል አማካኝነት መሆኑን ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሌሎች አገሮች አቻዎቻቸውና ዲፕሎማቶች እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም ሚኒስትሩ ከሩዋንዳ አቻቸው መወያየታቸውንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋርም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን በተለይም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከሰሩ የሚፈለገውን ማድረግ እንደሚቻል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ወረርሸኝን ተከትሎ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸው፤ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ዜጎች ከቤት እስከመውጣት መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በየአገራቱ ከሚገኙ ቆንስላዎች፣ የኮሚኒቲው ማህበራትና ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ደርጅትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምግብ፣ የመጠለያና የህክምና አገልግሎት እንዱያገኙ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አንስተዋል።

መመለስ የሚሹትን ደግሞ ወርርሽኙን ሊያባብስ በማይችል መንገድ እንዲመለሱና በአገር ቤት የሚቋቋሙበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሰራመሆኑንም ገልጸዋል።

በጦርነት ውስጥ በምትገኘው የመን ዜጎችን የመደግፍ ስራው ከባድ እንደሆነ ገልፀው፤ ያም ሆኖ መንግስት ከተመድ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

እስካሁንም ከቤይሩት፣ ከአቡዳቢ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከኩዌት እንዲሁም ከተለያዩ ጎረቤት አገሮች 30 ሺህ 87 ዜጎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለስን ጨምሮ በያሉበት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በመደገፍ በዜጋ ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ግንኙነት ርዕሰ ጉዳዮች ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

በተለይም ግድቡን አስመልክቶ በሚደረጉ የድርድር ነጥቦች በኢትዮጵያና የግርጌ ተፋሰስ አገሮች መካከል ስላሉ የልዩነት ነጥቦችን በዝርዝር አስረድተዋል።

ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ እንደ ዘንድሮው በቂ ዝናብ ብታገኝ በ3 ዓመታት ግድቡን እንደምትሞላ፣ ካልሆነ ግን ከ4 እስከ 7 ዓመታት ጊዜ መሙላት እንደምትችል ስትገልጽ፤ ሌሎቹ ደግሞ እስከ 20 ዓመት የመለጠጥ ፍላጎት እንደሚያነሱ ገልጸዋል።

የድርቅ ጊዜ ስምምነትን በተመለከተም ኢትዮጵያ የታችኞቹ አገሮች የድርቅ ሁኔታ ታሳቢ እንደምታደርግ ስትገልፅጽ፤ በአንጻሩ የግርጌ ተፋሰስ አገሮች ከግድቡ ምን ያህል የውሃ መጠን ይለቀቃል በሚለው ላይ ትኩረት እንደሚያድርጉ ገልጸዋል።

በስምምነቱ ላይ የታችኞቹ ተደራዳሪዎች ገዥ ወይም አሳሪ ውል የሚሹ ሲሆን በአንጻሩ ኢትዮጵያ ካለው እውነታ ጋር እየታየ የሚለዋወጥ አጠቃላይ ስምምነት እንደምትሻ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም