የግድቡ ውሃ ሙሌት የመጀመሪያው ስኬት ቀጣዩን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሚያነቃቃ ነው -ድሬዳዋ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ውሃ ሙሌት የመጀመሪያው ስኬት ቀጣዩን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሚያነቃቃ ነው -ድሬዳዋ አስተዳደር
ድሬዳዋ ሐምሌ 17/2012( ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የመጀመሪው ስኬት ቀጣዩን ግንባታ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ከዳር እንዲያደርሱ የሚነቃቃ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።
የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ አስመልክቶ የምስጋናና ድጋፉን ለማጠናከር የሚያግዝ ዝግጅት በድሬዳዋ አስተዳደር ተካሄዷል፡፡
በዝግጅቱ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ መላውን ዜጋ ያስደሰተና የአንድነት ፍሬ ውጤት መሆኑን ያስመሰከረ ነው።
ይህም ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ጉዞ የሚመራውንና በአለም አደባባይ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለሚያደርገው ግድብ ድጋፋቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያጠናከሩ አስታውቀዋል፡፡
ለቀጣዩ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል እንዲፈጥር የግድቡ የውሃ ሙሌት ዋጋን ከፍ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡
ድሬዳዋን የምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ዕውን እንደሆኑ አንድነታችንን አጠናክረን መረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ፍትህ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሣ ጣሃ ሀገር ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ነቅቶ በመጠበቅ የተጀመረውን የድል ጉዞ ዳር ለማድረስ የፍትህና ፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለተገኘው ውጤት ሌት ተቀን እየለፉ ለሚገኙ ሁሉ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ናቸው።
ከአሁን በኋላ ግድቡ በማንም ኃይል ወደ ኋላ እንደማይመለስ ተናግረው ፖሊስም የህዝብን ሰላምና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተጓዳኝም የኮሚሽኑ አመራሮች ፣አባላትና ሠራተኞች ድጋፋቸውን ለማጠናከር በወር ደመወዛቸው ቦንድ መግዛት መጀመራቸውንም አመልክተዋል።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፍትህ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት የምስጋናና ድጋፍ ማጠናከሪያ ስነስርዓት የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የኮሮና ወረርሽን በመከላከል ለግድቡ ዳር መድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡