ቀጥታ፡

ሠራተኞቹ የኮቪድ-19 ተጽዕኖ በመቋቋም ለአየር መንገዱ ስኬት መስራታቸው ኩራት መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን አየር መንገድ ሰራተኞች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተጽዕኖ በመቋቋም ለአየር መንገዱ ስኬት መሥራታቸው ኩራት መሆኑን ገለጹ።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ እንዲተጋም ጥሪ አቅርበዋል።

አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ይዞ በዓለም አደባባይ ሲበር ስኬቱም በከፍታ ታጅቦ ዛሬ ላይ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ግዙፍ አየር መንገዶች ደግሞ 4 ተኛ እርከን ላይ ይገኛል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ አየር መንዶች በረራዎችን በማቆም እስከመዘጋት ሲደርሱ እና ሠራተኞቻቸውን ሲያሰናብቱ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱን ስትራተጂ ነድፎ የካርጎ አገልግሎት በመስጠት አስቸጋሪውን ወቅት በድል እየተወጣ እንደሆነ ይታወቃል።

በካርጎ አገልግሎቱ ከሚያጓጉዘው የንግድ ቁሶች በተጨማሪ በብቸኝነት ለ54ቱም የአፍሪካ አገሮች የኮቪድ-19 የህክምና ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ አለኝታነቱን አሳይቷል።

ለዚህም ስኬቱ የአመራር ሰጪውና የሠራተኞች ቁርጠኝነት መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ዜጎች በሁሉም የስራ መስክ ሊተጉ እንደሚገባ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

የበረራ አስተናጋጆች የቡድን መሪ ወይዘሮ ፍሬህይወት ወልደስላሴ እንደገለጹት፤ ቀድሞም ቢሆን አየር መንገዱ በጠንካራ የሥራ ተነሳሽነቱ ምሳሌ ነው።

አሁን በተከሰተው የዓለም ዓቀፍ የቀውስ ጊዜ በርካታ አየር መንገዶች በራቸውን ሲዘጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነበረበው ጠንካራ የሥራ ባህል ችግሩን ወደ እድል በመቀየር በስኬት እያለፈው እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ይህ ስኬት የኢትዮጰያን ከፍታ ለማረጋገጥ ጅማሮ ነው በማለት ሁሉም በተሠማራበት የሥራ መስክ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩን ወክሎ እንደሚሠራ በማሰብ ሊተጋ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአገር ከፍታ የሚረጋገጠውም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤት ሲያመጣ እንደሆነ በመጠቆም።

በአየር መንገዱ የገቢ እቃዎች ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሄም አቤል በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ በአስቸጋሪ ወቅት በአፍሪካና በዓለም የኮቪድ- 19 የህክምና ቁሳቁስ ሲያጓጉዝ መቆየቱን አንስተዋል።

የአየር መንገዱን ስኬት ለማስመዝገብ ሁሉም የሥራ ክፍሎች በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ይህም አበርክቶ እንደ አገር የሚቆጠር በመሆኑ የተሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ሰራተኞች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተጋላጭነት ለመቀነስ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በሚሠሩት ሥራ ውጤት ማምጣት በመቻላቸው እንደ ኢትዮጵያዊ የሚኮሩበት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

''ሁሉም ዜጋ በግሉ ለማደግና ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት እንደ አገር ሲታሰብ ደግሞ ለለውጥ በመሆኑ፣ የአገርን ፍቅር በሥራና በተግባር ማሳየት ይሻል'' ብለዋል ወይዘሮ ቤተልሄም።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የ'ካቢን ጥገና ቴክኒሻን' አቶ ዮናታን ጸጋዬ በሰጡት ሃሳብ ደግሞ ''ስኬት መጨረሻ ስለሌለው ሁሌም ወደ ከፍታ ማሰብና መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው'' ብለዋል።

አየር መንገዱ በኮቪድ-19 ከደረሰበት ጫና ተላቆ ወደ ቀድሞ ቁመናው ለመመለስ እየሠራ መሆኑንና ለዚህም የአንድ አመት ጊዜ ብቻ እንደሚወስድበት መግለጹ ይታወሳ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም