የጀርመኑ ቮይት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ተቋም በኢትዮጵያ ማዕከሉን ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመኑ ቮይት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ተቋም በኢትዮጵያ ማዕከሉን ከፈተ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 የጀርመኑ ቮይት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ተቋም በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ዘጠኝ አገሮችን የሚያስተሳስር ማዕከል በኢትዮጵያ ከፈተ። ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ግሩፕ የሆነው 'ቮይት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኩባንያ' በመላው ዓለም ከ60 በላይ ማዕከላት አሉት። ኢትዮጵያ ባላት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ብቃት፣ እያስመዘገበች ባለው ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገትና በስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ምቹነቷ እንዲሁም ለተጠቃሚዎች ያላት ቅርበት ማዕከል ሆና እንድትመረጥ ምክንያት ሆኗል። በኢትዮጵያ ማዕከል መክፈቱን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀ መርሃ ግብር የተገኙት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና፤ ኩባንያው ማዕከሉን በኢትዮጵያ መክፈቱ ዘርፉን ለማልማት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፆ ይኖረዋል። 'ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ኃይል ሀብት አብዝተው ከታደሉ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ናት' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አገሪቱ የታዳሽ ኃይልን በማስፋፋት የምታደርገውን ጥረት በማሳደግ በምስራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ማዕከል ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል። የማዕከሉ መከፈት ዘርፉን ለማልማት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አልፎ በዘርፉ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በኩባንያው ተቀጥረው የመስራት እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሚስስ ብሪታ ቫግነር በበኩላቸው፤ 'ኢትዮጵያ የጀርመን መንግስትና የጀርመን ኩባንያዎች አጋርና እውነተኛ ወዳጅ አገር ነች' ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ተወዳዳሪና ሳቢ የሆነ የቢዝነስ አካባቢ ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ጀርመን እንደምትደግፍ የገለጹት አምባሳደሯ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። የቮይት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚና የኮርፖሬት ማኔጅመንት ቦርድ አባል ኡዊ ቬንደርሀርድት እንደገለፁት፤ የማዕከሉ በኢትዮጵያ መከፈት በምስራቅ አፍሪካ ላለው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል። ኩባንያው ከ1940ዎቹ ጀምሮ በአፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ ማመንጨት ስራን ሲደግፍ መቆየቱን ያወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኩባንያው ለታዳጊና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ለሚገኙ አገሮች የኢነርጂ መሰረተ ልማት ግንባታ አጋር እንደሚሆንም ተናግረዋል።