ቀጥታ፡

የኢንቨስትመንት አማራጭ ስትራቴጅክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው

አሶሳ፤ ሐምሌ 17 / 2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚፈጠረውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመጠቀም ስትራቴጂክ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ለኢዜአ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ ከሀገራዊ ፋይዳው ባሻገር ለክልሉ የሚሰጠው የኢንቨስትመንት አማራጭ ሰፊ ነው፡፡

ይህን እድል ለመጠቀም ክልሉ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ስትራቴጂክ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂክ እቅዱ በአካባቢው የሚፈጠረውን ሀይቅ ተከትሎ ቱሪዝም፣ ዓሳ ሃብት፣ ትራንስፖርት እና ሌሎችንም ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በረጅም እና አጭር ጊዜ ምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተዘጋጀ የሚገኘው ስትራቴጅክ እቅዱ ሀይቅ ካላቸው የሃገሪቱ አካባቢዎችን ተሞክሮ መሠረት ያደረገ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ስራ ከመጀመሩ በፊት ውሃ በሚተኛበት ስፍራ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም በፈቀደ መሠረተ ልማት በማሟላት ወደፈለጉበት አካባቢ ለማሰባሰብ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ስትራቴጂክ እቅዱም እነዚህን  የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች በዘላቂነት ማሻሻል የሚቻልበትን እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም በበኩላቸው የክልሉ ህዝብ ከለውጡ በኋላ በህዳሴው ግድብ ቅድሚያ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

በቅርቡ ውሃ የሚተኛበትን ስፍራ የደን ምንጣሮ በማካሄድ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ስራአጥ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ኤጀንሴው ከክልሉ ስትራቴጅክ እቅድ በመነሳት በህዳሴው ግድብ አካባቢ የስራ እድል ለመፍጠር አቅጣጫ መቀመጡን  አቶ በሽር ገልጸዋል፡፡

ግድቡ በክልሉ መገኘቱ ትልቅ የኢንዱስትሪ አቅም እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አልማሂ ናቸው፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች እና የንግድ እንቅስቀሴም እንደሚነቃቃ ገልጸው ይህን ዘርፍ ለማጠናከር ቢሮው ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዝ ሰው ሰራሽ ሃይቅ የሚፈጠር ሲሆን ከ40 በላይ ደሴቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም