የሶስትዮሽ ድርድሩ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ስኬት ነው ... የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

68

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2012(ኢዜአ) ''የሶስትዮሽ ድርድሩ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ስኬት ነው'' ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና በዜጋ ዲፕሎማሲ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
የግድቡን ውሃ ሙሌት አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከፈለጉ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ለዓለም ያሳዩበት ነው።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የተካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ተካሂዶ ውጤታማ መሆኑ 'የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይቻላል' የሚለውን ሀሳብ የሚደግፍ ስኬት እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የyዲፕሎማሲ ተግባር መከናወኑን ገልጸው፤ በኮቪድ-19 ምክንያት ስራዎቹ የተካሄዱት በዌቢናርና በቨርቹዋል አማካኝነት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ከመካከለኛው ምስራቅና አጎራባች አገሮች ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለስን ጨምሮ በያሉበት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በመደገፍ በዜጋ ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም