በትግራይ ለአካል ጉዳተኞችና ለኮሮና ለይቶ ማቆያ ማእከላት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ለአካል ጉዳተኞችና ለኮሮና ለይቶ ማቆያ ማእከላት ድጋፍ ተደረገ
ሽሬ እንዳስላሴ/ መቀሌ ሐምሌ 17/2012 (ኢዜአ ) በትግራይ ክልል ለጦር ጉዳተኞች ማህበር አባላትእና ለሁለት የኮሮና ቫይረስ መከላከል ለይቶ ማቆያ ማዕከላት የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረገው ኤን አር ሲ የተባለ መንግስታዊ ያልሆን ግብረ-ሰናይ ድርጅት ተቋም መሆኑም ተመልክቷል።
ከተደረገው የቁሳቁስ ድጋፉ 1 ሺህ 500 ብርድ ልብስ ፣ 5 ሺህ የምግብ ማቅረቢያ ሳህኖች ፣ ማብሰያ ብረት ድስቶች ፣ 750 አንሶላዎችና የንጽህና መጠበቂያዎች መሆናቸውን የድርጅቱ ተወካይ አቶ ገብረዋህድ ገብረመድህን ገልጸዋል።
"አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ግምት ያላቸው እነዚህ ቁሳቁሶች የተለገሱት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ለመወጣት በማሰብ ነው" ብለዋል።
"ቁሳቁሶቹ በሽሬና ሽራሮ ለሚገኙ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ለይቶ ማቆያ ማዕከላት አገልግሎት የሚውሉ ናቸው"ብለዋል።
ድርጅቱ ያደረገውን የቁሳቁስ ድጋፍ የተረከቡት በትግራይ የሰሜን ምዕራብ ዞን አተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ሀጎስ ደስታ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ በክልሉ ለሚገኙ የጦር ጉዳተኞች ማህበር አባላት እንዲውል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ጨርቆስ ወልደ ማሪያም እንደገለጹት፤ ድጋፉ አካል ጉዳተኞቹ የምግብ ፍጆታቸውን በመሸመት በቤታቸው በመቆየት እንዲጠቀሙና የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚረዳቸው ነው።
በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በቤት ለመቆየት እንዲችሉ የምግብ ፍጆታዎችን የሚገዙበት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን የተናገሩት አካል ጉዳተኛ በሪሁ መለሰ ናቸው።
እንደልብ መንቀሳቀስ በማይቻልበት በዚህ ወቅት የተደረገላቸው ድጋፍ ስጋታቸውን ያቃለለ መሆኑንም ተናግረዋል።