ግብጽ የምታሰማውን የተዛባ ትርክት ለመቀየር ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ይከናወናል - ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ የምታሰማውን የተዛባ ትርክት ለመቀየር ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ይከናወናል - ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ላይ እያሰማችው ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ ።
ግድቡ ከኃይል ምንጭነት በተጨማሪ የወንዙን ጂኦ ፖለቲካ የቀየረ መሆኑም ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የስራ አስፈጻሚ አባላት ዛሬ ባካሄዱት መደበኛ ስብሰባ ነው።
በመድረኩ የግድቡ ክዋኔ ሪፖርት እንዲሁም የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የ2012 ዓ.ም አፈጻጸም ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
የስራ አስፈጻሚ አባላቱ በዚህ ወቅት በተለይ ግብጽ በግድቡ ዙሪያ እያከናወነች ያለውን የተዛባ ትርክት ማስተካከል እንደሚገባ ነው ያነሱት።
ግብጽ ግድቡን ዓለም አቀፍ የጸጥታ ስጋት አድርጋ በማቅረብ በተለይ የዓረብ አገራትን ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሰራች መሆኑም ነው የተገለጸው።
ስለ ግድቡ የሚደረጉ የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በመምራት የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም ለዓለም ማስረጽ እንደሚገባም ነው አባላቱ ያስገነዘቡት።
በተናጠል የሚሰራ የኮሙኒኬሽን ስራ መጠራጠርን እንደሚፈጥር በማስገንዘብ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በዓለም ላይ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ተሞክሮ የሚያሳየው የላይኛው ተፋሰስ አገራት ወንዙን በመጠቀም ደረጃ የተሻለ ዕድል እንዳላቸው አብራርተዋል።
በዓባይ ወንዝ የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒ የታችኛው ተፋሰስ አገር በተለይ ግብጽ ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም አባዜ መሆኑን ነው የገለጹት።
ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ኃይልን ከመስጠት በተጨማሪ ይህን የተዛባ የውሃ ጂኦ-ፖለቲካ መቀየሩንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ማንንም ለመጉዳት ሳይሆን መብራት አይተው የማያውቁ ዜጎቿን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የያዘችውን ሃቅ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስረዳቱ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው።
ከዚህ በተጓዳኝ በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር መሰራት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።
ግድቡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ አንጻር የግድቡን ደህንነት የሚያስጠብቁ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ግድቡ ይዟቸው የመጡ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመጠቀም ከወዲሁ በተደራጀ መልኩ እንዲሰራም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከአምስት ሄክታር በላይ የሚሰፉ ከ70 በላይ ደሴቶች ይፈጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።