ተቋማቱ የምርት ጥራትን ማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ የምርት ጥራትን ማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የደረጃዎች ኤጀንሲ በምርት ጥራትና ማሻሻያዎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
የሚኒስቴሩ የጥራት የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው አገር አቀፍ የምርት ጥራት ደረጃ እንዲኖር ለማድረግ ስለተሰሩ ስራዎች አብራርተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ 11 ሺህ 800 የጸደቁ እንዲሁም 170 አስገዳጅ ደረጃዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በማር እና በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
እነዚህ ምርቶች ዓለምአቀፍ ገበያ ውስጥ ሰብረው እንዲገቡና በዓለም አቀፍ ቋንቋ መግባባት የሚችሉ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።
የደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንንም የኮሮና ወረርሽኝ ኢኮኖሚው ላይ በተለይም ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በመፍጠሩ ይህን ለመከላከል የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው የደረጃዎች የፍላጎት ዳሰሳ በማድረግ በተለዩ ዘርፎች ላይ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚያስፈልጉ ደረጃዎች ተለይተዋል ብለዋል።
ይህን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ምርት በየትኛውም ዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ኤጀንሲው ደረጃዎችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ለማድረግም የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግና ይህም የማምረቻ ተቋማት፣ ላኪዎችና አምራቾች እመርታ እንዲያመጡ እንደሚያግዝ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በቀጣይ ዓመታትም ኤጀንሲው 216 ደረጃዎችን በተለያየ ጊዜ ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል።
የጥራትና ማሻሻያ ስራ ለመስራት ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱም በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።