የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ድጋፋቸውን ለማጠናከር እንዳነቃቃቸው በድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ድጋፋቸውን ለማጠናከር እንዳነቃቃቸው በድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ድጋፋቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንዳነቃቃቸው በድሬዳዋ አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት የግድቡ የውሃ ሙሌት የመጀመሪያው ስኬት ሀገሪቱ የጀመረችው የዲፕሎማሲ ድርድር ውጤታማ የሚያደርግና ተቀባይነቷን የሚያሳድግ ይሆናል፡፡
ወይዘሮ ከድጃ አሊ በድሬዳዋ አትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ግድቡ ውሃ መያዙ በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ ይህም ድጋፋቸውን ለማጠናከር መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ወጣት ሰለሞን ታያቸው በበኩሉ "ግድቡ እንደተሸጠ የሚናፈሰው ወሬ ውሸት ሆኖ በማየቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ሲል ተናግሯል።
ከመንግስት ጋር በመሆን ግድቡን እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ግድቡ አሁን ውሃ ይዞ ማየት በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና በዚህ በመነቃቃትም ለግንባታው ድጋፋቸውን በማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አይናለም በቀለ ናቸው፡፡
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ዮሃና ገዛኻኝና እናቷ ወይዘሮ መርሻ ኪዳኔ ግድቡ በውሃ ተሞልቶ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ወይዘሮ ማስረሻ ለዓመታት በነበረው የግድቡ መጓተት ተስፋ ቆርጠው እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የሚያደርጉትን ድጋፍ በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም ቦንድ በመግዛት ለማጠናከር እንዳነቃቃቸው ተናግረዋል፡፡
"ዛሬ ሀገራችን አንድ ታላቅ ድል እንደተቀዳጀች ተሰምቶኛል፤ ወደ ልማትና ብልጽግና ለመጓዝ የሚያስችለን ፍንጭ ተፈጥሮልናል " ያሉት ደግሞ አቶ አሊ መሐመድ ናቸው፡፡
ከአሁን በኋላ የተጀመረው የድል ጉዞ እንደማይደናቀፍ ገልጸው፤ ወጣቶች የሀገር አጥፊዎችን መንገድ በመጠየፍ ልማትና ሰላም ላይ መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ታዬ ኢትዮጵያ የተፈጠረባትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተቋቁማ ግድቡን ለዚህ ደረጃ ማብቃቷ ሁሉንም የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በሁሉም መስክ የጀመረውን ሥራ ከማጠናከሩ በተጓዳኝ ዛሬ መነቃቃት የፈጠረውን ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲጠናክር መስራት አለበት ብለዋል፡፡