ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ትምህርት እንደገና ለማስጀመር ግንኙነትን ማጎልበት ያስፈልጋል--የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት እንደገና ለማስጀመር ከጤና ተቋማትና አጋር አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት እንዳለባቸው የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ተቋማቱ ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል የተደረገው ዝግጅት ለመንግሥት ቀርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ ነው ይላል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተቋርጦ የነበረውን የተቋማቱ ትምህርት ዳግም ለማስጀመር የሚደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ዓለም የንግድ ተቋማትን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

የወረርሽኙን ስርጭት ገምግመው እየቀነሰ መሆኑን የተረዱ አገሮች ትምህርት ቤቶችን ቢከፍቱም፤ በማገርሸቱ መልሰው ለመዝጋት ሲገደዱ ተስተውሏል።

በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል ባለብዙ ዘርፍ ተሳትፎ ቡድን አባል ወይዘሪት ራሄል ለማ እንዳሉት አገሮች ትምህርት ቤቶችን የሚከፍቱት የበሽታው ስርጭት መቀነስ ሲጀምር ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወረርሽኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመሆኑ መቼ የመጨረሻው ስርጭት ላይ እንደሚደርስ በትክክል አይታወቅም ብለዋል።

ወረርሽኙ ከተከሰተበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ጀምሮ እስካሁን ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥርም

ከ 0 ነጥብ 3 በመቶ እንደማይበልጥም ገልጸዋል።

በመሆኑም የተቋረጠውን ትምህርት በተቋማቱ እንደገና ለመጀመር ከጤና ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መፈተሽ አለባቸው ብለዋል።

ከፖሊሲና እንዲሁም የዕድሜና ተጓዳኝ የጤና እክል ያለባቸውን የተቋማቱን ማኅበረሰብ አባላት ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ተቋማት የራሳቸውን ዝርዝር እቅድ እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።

ዕቅዱ በሽታውን ለመከላከል በሚያስችል መንገድ መዘጋጀቱንና የተጋላጭነት ሁኔታው ለመንግሥት ቀርቦ ፈቃድ ሲያገኝ ተማሪዎችን ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች በበኩላቸው ተቋማቱ የኮቪድ-19 ሕክም ማዕከላት ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋማቱ ማገገሚያ፤ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ሆነው ስለሚያገለግሉ በቀላሉ ለትምህርት ዝግጁ ማድረግ ከባድ እንደሆነ አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ተማሪዎች የሚገባቸውን እውቀት ገብይተው ወደ ቀጣዩ ደረጃ መሸጋገር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም "በተለየ ሁኔታ የተለየ ዝግጅት በማድረግ ትምህርቱንም በተለየ ሁኔታ መስጠት ይጠይቃል" በማለት አሳስበዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርቱን የጨረሱ ተማሪዎች በሰባት ቀናት፤ ከ51 እስከ 75 በመቶ የተማሩ በ20 ቀናት፤ 20 በመቶ የቀራቸው በ45 ቀናት፤ እንዲሁም የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት ያልጨረሱና ሁለተኛውን ያልጀመሩ በሁለት ወራት ማጠናቀቅ እንዲችሉ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም