"የግድቡ የውሃ ሙሌት በወንዙ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት የዘለቀው ኢ-ፍትሃዊነት ማብቃቱን ያበሰረ ነው"--ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
"የግድቡ የውሃ ሙሌት በወንዙ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት የዘለቀው ኢ-ፍትሃዊነት ማብቃቱን ያበሰረ ነው"--ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት የዘለቀው ኢ-ፍትሃዊነት ማብቃቱን ያበሰረ ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
"በግድቡ ግንባታ ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን አልፈን እዚህ እንድንደርስ ህዝባችን የማይተካ ሚና አበርክቷል" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ትናንት ይፋ መሆኑ ይታወሳል።
ከዚህ ታሪካዊ ዕለት ማግስት የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አባላት መደበኛ ስብሰባቸውን አድርገዋል።
በመድረኩም የግድቡ ክዋኔ ሪፖርት እንዲሁም በግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የ2012 አፈጻጸም ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
የግድቡን ክዋኔ ሪፖርት ያቀረቡት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ "ኢትዮጵያ ከ160 ሺህ ጌጋ ዋት ሀወር በላይ መልማት የሚችል አቅም ቢኖራትም ከዚህ ውስጥ መጠቀም የቻለችው 10 ከመቶ አይበልጥም" ብለዋል።
"የህዳሴ ግድቡም በቀጣይ ያለንን አቅም በመጠቀም ደረጃ ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
የግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ትልቅ ብስራት መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ዓመት የካቲትና መጋቢት ወራቶች ሃይል የማመንጨት ስራ በሙከራ ደረጃ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ሰኔ ወር ላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሃይል የማመንጨቱ ስራ ሙሉ ለሙሉ ይጀምራል ነው ያሉት።
ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣይ በበጋ ወራቶች የ11 ተርባይኖች ገጠማ እንደሚከናወንም ነው ያነሱት።
ግድቡን በሚመለከት በተደረገው የሦስትዮሽ ውይይት በአበይት ጉዳዮች ከስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
በሁሉም ደረጃ የሚከናወነው የውሃ ሙሌት ጉዳይ በአጭር ጊዜ በመግባባት እንዲፈታ እንዲሁም የውሃ አጠቃቀምን ጨምሮ የሚነሱ ጉዳዮች ዘላቂና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለወደፊት በድርድር እንዲቋጩ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ነገር ግን ግብጽ ግድቡ የሚይዘውን ውሃው "በጋራ እናስተዳድር" የሚል አቋም አንዳንጸባረቀች ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ ሳታሳርፍ ውሃውን በሉዓላዊነት የማስተዳዳር አቋም እንዳላትም ነው የገለጹት።
የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የግድቡ ግንባታ ላይ የዜጎችን ተሳትፎ ለማነቃቃት የተለያዩ ዲጂታል ስልቶችን ቀይሰን ተንቀሳቅሰናል ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ መከሰት የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮች እንዳይካሄዱ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸው፤ በዚህ ችግር ውስጥም ሆነን ከ744 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ችለናል ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በመጠቆም።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው "የግድቡ ግንባታ በርካታ ታሪካዊ ሂደቶችን በማለፍ ሁላችንም ወደምንጓጓለት ምዕራፍ ተሸጋግሯል" ብለዋል።
የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ፤ የወንዙ ፍሰት አቅጣጫ የተቀየሰበት፤ በግድቡ ግንባታ ተፈጥረው የነበሩ እንከኖች የተቀረፉበትና የመጀመሪያው ምእራፍ ውሃ ሙሌት የተጠናቀቀበት ዕለት በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ታሪካዊ ምዕራፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዓለም ላይ በኢ-ፍትሃዊነት ከሚታወቁት ጉዳዮች አንዱ የአባይ ወንዝ አጠቃቀም መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በግድቡ እየተከናወነ ያለው ስራ ኢ-ፍትሃዊነት ማብቃቱን ያበሰረ መሆኑን አብራርተዋል።
"በግድቡ ግንባታ ወቅት የገጠሙን ፈተናዎችን ተሻግረን እዚህ እንድንደርስ ህዝባችን ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ለዓለም ማህበረሰብ በማስገንዘብ ደረጃ ጉልህ ሚና መጫወታቸውንም ነው ያወሱት።
የግድቡን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ አሁንም በአንድነትና በጋራ መቆም ይገባል ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።