በባህር ዳር ከተማ የመሰረተ ልማት ተቋማት ምረቃና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ተግባር ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ የመሰረተ ልማት ተቋማት ምረቃና የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ተግባር ተከናወነ
ባህር ዳር ሐምሌ16/2012 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማን ዘመኑን የሚመጥን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች ከተሞችም አርአያ ሊሆን የሚገባ ተግባር ነው ሲሉ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመደ ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2012 ዓ.ም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ 57 ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን ከ760 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነቡ አዳዲስ ተቋማት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በፕሮግራሙ የተገኙት ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ እንደገለጹት ባህር ዳር ከተማ ተፈጥሮ ያደላትን ውበት በማስፋት ጽዱና ማራኪ ከተማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች ከተሞችም በአርአያነት የሚወሰድ ነው።
በተለይ ነጋዴውን ማህበረሰብ በማሳመን ምትክ ቦታ በመስጠት ሊገነባ የታቀደው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ህንጻ ህብረተሰቡና አመራሩ ተናቦ እየሰራ እንደሆነ በተጨባጭ ያመላክታል ብለዋል።
ይህ የገበያ ማዕከል ፍጻሜ ላይ ደርሶ የልምድ መቀመሪያ ማዕከል እንዲሆን የኮንስትራክሽንና ቤቶች ሚኒስትር በሚችለው ሁሉ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ከተሞች የወደፊት እድገታቸውን መሰረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አመልክተው ለዚህም በባህር ዳር ከተማ መጭውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን የማሟላት ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በተላይም ህግን የማስከበር ተግባራት በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን አመልክተው የከተማዋን ገጽታ የሚያዳብሩ ዘመናዊ ግንባታዎችን እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት የተመረቁትና ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የአስፓልት፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ፣ የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የንግድ ሸዶችና መሰል ግንባታዎች ይገኙበታል።
እነዚሁ ግንባታዎች የከተማዋን የወደፊት የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና ምቹ የመኖሪያ ከተማነትን ይዛ እንድታድግ በሚያስችል አግባብ መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይ ዓመታትም ከ760 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከሁለት ሺህ በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስቆም የሚችል ዘመናዊ የገበያ ማዕከል፣ ባለ 20 ወለል የከተማ አስተዳደሩ ቢሮ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤትና የክፍለ ከተሞች ጽህፈት ቤት ግንባታዎች ይገኙበታል።
የሚገነባው የገበያ ማዕከል አንድ ነጥብ ስድስት ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን መዝናኛ ፋፏቴን ጨምሮ ከአውሮፓ ሀገራት በተወሰደ ልምድ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪም በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈውና 270 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት ባለስምንት ፎቅ የገቢዎች ሚኒስትር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ቢሮ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
ባህር ዳር ከተማ በተፈጥሮ በአባይና ጣና ተከባ የምትገኝ ውብ ከተማ ብትሆንም እስከ አሁን በተፈጥሮ የታደለችውን ያክል ማልማት እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
አሁን ግን አመራሩ ከተማዋን ከሌሎች አለም አቀፍ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ለዚህም ህብረተሰቡን የማወያየትና የማግባባት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ።
በምረቃና የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ፕሮግራሙ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ሚኒስትሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።