ቀጥታ፡

ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ግንባር ቀደም ሃላፊነታውን እንደሚወጡ አመራሮች ገለጹ

አሶሳ ሐምሌ 16 / 2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲጠናክር ግንባር ቀደም ሃላፊነታውን እንደሚወጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

የግድቡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማስቆም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አመራሮቹ ገልፀዋል ።

ሰሞኑን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ተገኝተው ጉብኝት ካደረጉ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አቶ አብዱልሙኒዬም አደም ለኢዜአ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ንብረት የሆነው የህዳሴው ግድብ ግንባታው ለፍጻሜ መቃረቡን በአካል ተገኝቼ ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአባይ ወንዝ ላይ በተደጋጋሚ ግድብ ለመገንባት ተሞክሮ አለመሳካቱን ያስታወሱት ከፍተኛ አመራሩ ይህም የግድቡን ስራ የማይቻል አስመስሎት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡን በአግባቡ በማስተባበር የማይቻል ነገር እንደሌለ የህዳሴው ግድብ በተግባር ማሳየቱን አቶ አብዱልሙኒዬም አስረድተዋል፡፡

ሌላው አመራር አቶ አሲር ኢብራሂም በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት እንደሆነ ገልፀው የዚህ ትውልድ አካል በመሆኔ እኮራለሁ ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን የግድቡን አካባቢ ሠላም በመጠበቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ከፍተኛ አመራሩም ፕሮጀክቱ ከፍጻሜ እንዲደረስ በማድረግ ላይ የአቋም ልዩነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ህብረተሰቡ በበለጠ ተገንዝቦ ድጋፉን እንዲያጠናክር ማድረግ እንዳለብን ይሰማኛል ሲሉ አቶ አስር አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ትክክኛ ሲሆን ሌሎችንም የተፋሰሱ ሃገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል ፡፡

ግድቡን ከጎበኙ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አቶ በሽር አብዱራሂም እንዳሉት ክልሉ የግድቡን ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ደን መንጥሮ ለማስረከብ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር ከገባው ውል ቀድሞ ስራውን አጠናቆ አስረክቧል፡፡

 የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ግንባታውን ለማስተጓጎል የውስጥ እና የውጪ ሃይሎች ህብረት ፈጥረው እየተንቀሳሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የክልሉ ህዝብ እና መንግስትም የግድቡ እና አካባቢውን ሠላም ከመቼውም በላይ ነቅተው እየጠበቁ መሆኑን ከፍተኛ አመራሩ ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ከፍተኛ አመራር አቶ መሃመድ አልማሂ ህብረተሰቡን ለግድቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድገፍ ሲያስተባብሩ መቆየታቸውን ገልጸው በሰሞኑ የግድቡ ጉብኝት ግንባታው የደረሰበት ደረጃ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡን የማስተባበር ግንባር ቀደም ሃላፊነታውን እንዲወጡ የበለጠ እንዳሳሳቸው እኚሁ ከፍተኛ አመራር ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ የህዳሴው ግድብን ለማደናቀፍ የሚደረገውን ሴራ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም