በይስማ ንጉስ ዘመናዊ ሙዚየም ተገነባ - ኢዜአ አማርኛ
በይስማ ንጉስ ዘመናዊ ሙዚየም ተገነባ
ደሴ፣ ሀምሌ16/2012(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አጼ ሚኒልክ ከጣሊያን ጋር የተፈራረሙበት "ይስማ ንጉስ " ታሪካዊ ቦታ ላይ 25 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ዘመናዊ ሙዚየም መገንባቱን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር "የውጫሌ ስምምነት" በመባል የሚታወቀውን ስምምነት ከ20 አንቀጾች መካከል በ17ኛው ላይ የትርጉም ለውጥ በማምጣቱ ለአድዋ ጦርነት መነሻ መሆኑ ይታወሳል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት የጦርነቱ መነሻ የሆነው የውጫሌ ስምምነትን የተፈራረሙበት ታሪካዊ ቦታን በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የይስማ ንጉስ ሙዚየም ግንባታ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው።
በክልሉ መንግስት፣ በዞኑ አስተዳደርና በህብረተሰቡ ድጋፍ ሙዚየሙ በተያዘለት ጊዜና ጥራት ግንባታው ተጠናቆ ሰሞኑን ርክክብ መፈጸሙን አስታውቀዋል።
ሙዚየሙ ሦስት ህንጻዎችን ያካተተ መሆኑን አመልክተው የኢትዮጵያን አንድነትና ታላቅነት አሻራ በሚገልጽ መልኩ መገንባቱን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የእርሻ ማሳውን በነጻ ከመስጠቱም ባለፈ የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ በጉልበቱ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
አሁን ላይ ሙዚየሙን ወደ ስራ ለማስገባት ታሪኩን የሚገልጹ ቅርሶችን ከፌደራልና ክልል መንግስት ጋር የማፈላለግ ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እየጎበኘ ታሪኩን ተረድቶ አንድነቱን፣ ፍቅሩንና አብሮነቱን ለማስቀጠል እንደሚረዳ የተናገሩት ኃላፊው ወጣቱ የጥንት አባቶችን ታሪክ አውቆ የሀገሩን ዳር ድንበር እንዲጠብቅ ያስችላል ብለዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የአንባሰል ወረዳ ቀበሌ ሶስት ነዋሪ አቶ መላኩ ፈንታው በሰጡት አስተያየት ቦታው ምንም እንኳ ለአደዋ ድል መነሻ ታሪካዊ ቦታ ቢሆንም ሳይለማ መቆየቱ ቅሬታ ፈጥረባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢው ታጥሮ ከእንሰሳት ንክኪ ነጻ ከመሆኑም ባለፈ የዘመናት ጥያቄያችን መልስ አግኝቶ ሙዚየም በመሰራቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ታሪክ እንዳይጠፋ በማሰብ ሩብ ሄክታር መሬታቸውን ያለ ካሳ በነጻ ለሙዚየሙ ግንባታ እንዲውል መስጠታቸውን የገለጹት ደግሞ የዚሁ አካባቢ ነዋሪ አቶ ያሲን አብደላ ናቸው፡፡
የውጫሌ ስምምነት የተካሄደበት ይስማ ንጉስ ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ታሪኩን ለማቆየት የአካባቢው ማህበረሰብ በየዓመቱ የአደዋን የድል በዓል በቦታው እያከበሩ እዚህ ደረጃ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የውጭ ዜጎች ጭምር ቦታውን መጎብኘት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
ሙዚየሙ ተገንብቶ ብቻ እንዳይቀር መንግስት ቁሳቁሶችን አሟልቶ መንገዱን በማስተካከልና አካባቢውን በማልማት ለቱሪስቶች ምቹ እንዲያደርግም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ለአደዋ ጦርነት የክተት ጥሪ አዋጅ ነጋሪት በተጎሰመበት ወረኢሉ ከተማም ተመሳሳይ ሙዚየም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ከዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡