በአንድ ወር ውስጥ በዶሮ እርባታው ዘርፍ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱ ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ወር ውስጥ በዶሮ እርባታው ዘርፍ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱ ተነገረ
ሀምሌ 16/2021 (ኢዜአ) ባለፈው አንድ ወር ብቻ ኮቪድ 19 ባስከተለው ጫና በዶሮ እርባታው ዘርፍ ላይ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኀበር ተናገረ፡፡
በተለይም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የገባውም የዶሮ ዘር በኪሳራ መሸጡ ተገልጿል፡፡
የዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኀበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገነነ ተስፋዬ አንደገለጹት በወረርሽኙ ምክንያት የተከሰተው የትራንስፖርት መስተጓጐል በዋናነት የዶሮና የእንቁላል ምርት በሚፈለገው ጊዜ ለገበያ እንዳይቀርብ አድርጎታል፡፡
ለገበያ ቀርቦ የነበረውም ምርት ኮሮና ባስከተለው የገበያ መቀዛቀዝ ከሽያጭ ውጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም 3ሺ ኪሎ ግራም የዶሮ ስጋ ከገበያ ውጪ ሆኖ መወገዱን አንስተዋል፡፡
ዘርፉ ከኮሮና በሽታ ጋር ተያይዞ በሚነሳበት የተሳሳተ መረጃም 50 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ተደራሽነቱን እንዳጣ ነው የተናገሩት።
በዚህም በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከውጪ የሚመጡትን የዘር ዶሮዎች የሚያባዙት ድርጅቶችም ከ22 ወደ ስድስት መቀነሳቸውን አስረድተዋል፡፡
የመኖ አቅርቦት ደግሞ ሌላው ዘርፉ የገጠመው ችግር ሲሆን የመኖ ዋጋ 20 በመቶ መጨመሩን ተናግረዋል።
በዚህ የተነሳ የአቅርቦት ችግር እየጨመረ መምጣቱንና ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ከመጪዎቹ አምስት ወራት በሗላ የእንቁላልና የዶሮ አጥረት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቁሟል።
መንግሥት የውጭ ምንዛሬና የግብር ቅነሳ ድጋፎችን በማድረግ ዘርፉን ከአደጋ እንዲታደገው ነው በመፍትሄነት የተመላከተው።
በአሁኑ ወቅት በዶሮ እርባታ ዘርፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተደራጅተው በስራ ላይ የሚገኙ ቢሆንም በመኖ እና በዘር እጥርት ምክንያት የሥራ ሕልውናቸው ለአደጋ መጋለጡን ከኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኀበር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡