ቀጥታ፡

የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የስራ ቦታን ምቹ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አሰራር ነው

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) ለማኅበረሰቡ መልካም አገልግሎት ለመስጠት የሠራተኛውን የስራ ቦታ ምቹ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አስራር መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባላት የባለሥልጣኑን ዋና መስሪያ ቤት የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

የባለሥልጣኑ ተቋማዊ አደረጃጀት ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችልም በጉብኝቱ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።

የተቋማትን መዋቅራዊ አደረጃጀትና አስራር ለማዘመን "የአመራር ቅንነት ያስፈልጋል" ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ይህን ቅንነት በመስሪያ ቤቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የባለሥልጣኑ አደረጃጀት ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ሊሆን የሚችል እንደሆነና ይህ መልካም ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ እያከናወናቸው ከሚገኙና ተምሳሌት ከሆኑት መካከል በሠራተኞች አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ግንዛቤ እንዲሁም ተቋማዊ አሰራርን በማዘመን ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

ሌሎች ተቋማትም ይህን በማየት የስራ ቦታቸውን ለሠራተኞቻቸውና ለተገልጋዮች ምቹ ማድረግ እንድሚገባቸው አመልክተዋል።

ተቋማት እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለማኅበረሰቡ አርዓያ መሆን አለባቸው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ ናቸው።

ባለሥልጣኑ የጀመረውን ተቋማዊ አደረጃጀት ወደ ሠራተኞቹ በማስረፅ አገር መቀየር የሚያስችል ኃይል ማፍራት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ለማኀበረሰቡ ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት የሠራተኛን የስራ ቦታ ምቹ ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው አሰራር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ተቋሙን በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ያስፈለገው 'ኅብረተሰቡን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ለማገልገል ነው' ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተጀመሩት ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ኢንጂነር ሀብታሙ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክተውም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሕዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት ስኬት የድህነት ተራራ እየተደረመሰ መሆኑን ያሳያል ያሉት ኢንጂነር ሃብታሙ ሕዝቡም አንድነቱን በማስጠበቅ ሌሎች ታሪኮችን ማስመዝገብ አለበት ብለዋል።

በጉብኝቱ የባለሥልጣኑ ተቋማዊ አደረጃጀት ለአገልግሎቶች አሰጣጥ ፅዱ እና ምቹ መሆኑን መመልከት ተችሏል።

የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ቅንነትን መሰረት በማድረግ ኅብረተሰቡን በማገልገል ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

የተቋሙን ታሪካዊ ዳራ እንዲሁም እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችን የሚገልፀውና በቴክኖሎጂ የተደገፈው ቋሚ ኤግዚቢሽንም ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም