ቀጥታ፡

በአፋር የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር አመራሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- አቶ አወል አርባ

ሰመራ፣ ሐምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) በአፋር ክልል የቆየው የህዝቦችን አብሮነትና ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አውል አርባ አሳሰቡ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች  በወቅታዊ  ጉዳዮች ዙሪያ  በመከረቡት ወቅት ርዕሰ  መስተዳድሩ እንደገለጹት  ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ በነበረው ሀሰተኛ ፌዴራሊዝም አፋር በሁለንተናዊ መስክ የተጎዳበት ነበር።

በዚህም በተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ልማት ስም ሰፊ ለም መሬቱና ሰፊ የማዕድን ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተመዘበረ የክልሉ ህብረተሰብ የበይ ተመልካች ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።

በፖለቲካው መስክም በፌዴራሊዝም ስም በሀገሪቱ በተዘረጋው የህወሓት አፋኝ ቡድን ክልሉ እራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር ከፍተኛ  ጣልቃ-ገብነት እንደነበረውም ጠቅሰዋል።

ይህንን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በማስወገድ የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እንዲረጋገጥ በውስጥና በውጭ ሲደረግ የነበረው ትግል ፍሬ አፍርቶ ዛሬ  በሀገሪቱ  እውነተኛ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ሀቀኛ ፌዴራሊዝም ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ውኅደት ከዚህ በፊት እንደ አፋር ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ክልሎች ተገልለውበት ከነበረው  ሀገራዊ አጀንዳዎች እኩል ተሳትፎና የመወሰን መብት የተረጋገጠበት ወቅት መድረስ መቻሉንም አቶ አወል ተናግረዋል።

ሆኖም የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማናፈስና የጥፋት መልዕክቶችን በማሰራጨት በክልሉ ሁከት ለመፍጠር ቢጥሩም  በህብረተሰቡ ተሳትፎ  ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ ያለውን ሰላም ፣ የህዝቦች አብሮነትና ወንድማማችነት ለማደፍረስ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር የክልሉ ጸጥታ ኃይል ከፌዴራሉ  ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የጥፋት ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ለውጡን በባለቤትንና በቁርጠኝነት በመምራት ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በአመራሩ ውስጥ ከሚስተዋሉ የጎጠኝነትና ጎሰኝት አመለካከቶች እራሳቸውን በማጽዳት ለክልሉን ህዝቦች  አብሮነትና ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊማ አቡበከር   ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው የፓርቲ መዋቅር  የሚስተዋሉ የአመለካከት ክፍተቶችን ለመሙላት አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ  ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አመራሩ ከጸጥታ መዋቅሩና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የክልሉን ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት ለማስቀጠል መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የመከሩት ትናንት በሰመራ ከተማ  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም