ቀጥታ፡

ለቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግብዓት የሚያቀርቡ ማዕከላት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ባሀርዳር፤ ሐምሌ16/2012(ኢዜአ) ለቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግብዓት የሚያቀርቡ ሰባት የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። 

በኮርፖሬሽኑ የጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ ነጋ ደምስ ለኢዜአ እንደገለጹት እየተገነቡ ያሉት የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሚመግቡ ናቸው።

ከእነዚህም 400 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው የሞጣ ሞዴል የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ግንባታ  ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋል ብለዋል።

ማዕከሉ የአስተዳደር፣ የሴቶች ሙያ መተግበሪያ፣ የጥናትና ምርምር፣ የላብራቶሪና 19 የምርት ማሳያና የመገበያያ ሱቆችን ያካተቱ  ሶስት ዘመናዊ ህንጻዎች ያሉት ነው።

ከግንባታውም የእንስሳት፣ የአትልክልትና ፍራፍሬ፣ የማርና ሰም፣ የወተትና እንቁላል መሰብሰቢያ፣ ማጣሪያ፣ ማከማቻና ማሸጊያ ሰባት ሼዶች  መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በግቢው ውስጥ ያለው የአስፓልትና ድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ የውሃ አቅርቦት፣ ግቢውን የማስዋብና ሌሎች ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በቀጣይም እስከ 200 ሚሊዮን ብር በሚጠይቅ ወጪ የማዕከሉን አደረጃጀት በመፍጠር፣ የሰው ኃይል፣ የማቀዝቀዣ፣ የላብራቶሪና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንደሚሟሉ አስረድተዋል።

ግንባታ በ2010 ዓ.ም  ከተጀመረው የሞጣ ሞዴል ማዕከል ልምድ በመውሰድም በፍኖተ ሰላም፣ ቻግኒ፣ እንጅባራ፣ ዳንግላ፣ መራዊና አማኑኤል ከተሞች ተመሳሳይ  ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሞጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ የሺዋስ አንዷለም በበኩላቸው ማዕከሉ መገንባቱ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና ባለሃብቶችን በመሳብ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን  ያግዛል ብለዋል።

ይህን በመገንዘብም ከዘጠኝ ሄክታር በላይ መሬት ከሶስተኛ ወገን ነጻ አድርጎ በማስረከብና ወሰን በማስከበር ለማዕከሉ ግንባታ መሳካት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ስራ ሲጀምርም በምርት ማሰባሰብ፣ በማጣራት፣ በማከማቸት፣ በማሸግና በማጓጓዝ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የእውቀትና ክህሎት ሽግግር በማምጣት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የታመነበት መሆኑንም አብራርተዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ ዳኜ ዋሴ እንዳሉት ለማዕከሉ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማቅረብ ከሶስት ዓመታት  በፊት ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የአርሶ አደሩን የአመራረት ዘይቤ በመለወጥም በሰብል ምርት ትርፍ አምራች እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።

በኮሪያ ልማት ድርጅት ፕሮጀክት በፎገራ ወረዳ እየተተገበረ የሚገኘውን በትንሽ መሬት ላይ የ" ግሬንሃውስ "የአመራረት ተሞክሮን በማምጣት 200 አርሶ አደሮች በቲማቲምና አትክልት ልማት መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።

ለማዕከሉ በቂ ግብዓት ለማቅረብ የሚያስችል በአባያና ጉማራ ወንዞች ላይ የክልሉ መንግስት በመደበው 400 ሚሊየዮን ብር የዘመናዊ መስኖ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

በአካባቢው ለሚገኘው ማዕከል ግብዓት ለማቅረብ የተሻለ ምርጥ ዘርና የዘር ብዜት በማካሄድ አርሶ አደሩን መደገፍ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ናቸው።

በዚህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅርበት ተቀናጅተን በመስራት በስልጠና ካበቃነው በአንድ ጊዜ የአመራረት ዘይቤውን ለመቀየር አስቸጋሪ አይሆንም ብለዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩንቨርሲቲ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሞጣ ሞዴል የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ግንባታ በቅርቡ መጎብኘታቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም