የቁንዝላ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክትን ሞዴል ለማድረግ እየተሰራ ነው

ባህርዳር ሃምሌ 16/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የቁንዝላ የተቀናጀ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቁንዝላ የተቀናጀ የአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ጉብኝትና ፓናል ውይይት ተካሄዷል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሆልቲ ካልቸር ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሃብታሙ እንዳሉት በአማራ ክልል ያለው አንጻራዊ ሰላም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።

በዚህም አምስት የኔዘርላንድ ባለሃብቶች በቁንዝላ የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት 500 ሄክታር መሬት በመረከብ በአበባ ልማት መሰማራታቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ  በአጠቃላይ ከሚለማው 1 ሺህ 530 ሄክታር መሬት ጋር ሲነጻጸር አንድ ሶስተኛው በቁንዝላ የሚገኝ ነው ተብሏል ።

 በቁንዝላ የአበባና አትልክልት ልማት ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የስራ እድል የመፍጠር እቅም እንዳለው ገልፀዋል ።

 የአበባ ልማት በሄክታር ለ30 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ተመራጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሆኑ በዘርፉ ላይ የሚነሱ በእውነታ ላይ ያልተመሰረቱ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በመመከት ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል ።

በቁንዝላ ፕሮጀክት የሚደገፉ የአካባቢው ወጣቶችና አርሶ አደሮችም በአለም ላይ ተፈላጊ በሆኑት የማንጎና የአቡካዶ ልማት መሰማራታቸው በቆጋ አካባቢ ከሚገኙ አርሶአደሮች ጋር በማስተሳሰር ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩበት ሁኔታ ይመቻቻል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለባለሃብቶች ምርጥ ዘር፣ አግሮ ኬሚካልና የእርሻ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ቁንዝላን ሞዴል የልማት ቀጠና ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ወንዳለ አስታውቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው ባለሃብቶች የሚያነሱትን የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የአስፓልት መንገድና ሌሎች ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ ነው።

ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ሃብት፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ የመጣ በመሆኑ በስራ እድል ፈጠራና በተሞክሮ ልውውጥ  የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኔዘርላንድ ባለሃብቶች መሬቱን ተረክበው ስራ በመጀመራቸው አመስግነው በቀጣይም አሁን ካሉበት የልማት እንቅስቃሴ በመፍጠን የተያዘውን ግብ ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ጌታሁን መኮነን እንዳሉት የቁንዝላ የተቀናጀ የልማት ፕሮጀክት "በጣና ግሪን መቀነት ልማት ኢንሸቲቭ" ከተያዙ 13 ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።

በዚህም የክልሉ መንግስት አራት ሚሊየን ብር በማውጣት የሻውራ ሳብስቴሽን በማስገንባት ባለሃብቶች የጠየቁትን የሃይል ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል።

የቴሌኮም ጥያቄው ተደራጅቶ ከቀረበ እንደሚፈታ ጠቁመው ከቁንዝላ ባህርዳር ያለው መንገድ አስፓልት እንዲሆን በስምምነቱ መሰረት ከፌደራል መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ተናገረዋል።

ወደ አካባቢው ለሚመጣው ሰራተኛ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም የከተማ ልማት ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን የአካባቢ ጥበቃ፣ ስድስት ቀበሌዎችን ያማከለ የገጠር ልማትና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልፀዋል።

የቁንዝላ ሆልቲ ፓርክ ፒኤልሲ ተወካይ ሚስተር ስሞን ሃሞንድ እንዳሉት የአጥር፣ የመኖሪያና ሌሎች ግንባታዎችን በማከናወን የአበባ ልማትን የማላመድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጭው ዓመት በስፋት ወደ ማባዛት በመግባትም ከቁንዝላ ባህርዳር ኤር ፖርት ያለው መንገድ በአስፓልት ደረጃ እንዲገነባና በቀጥታ ከባህርዳር ወደ ውጭ የሚልኩበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአበባ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ከ440 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም