ቀጥታ፡

ታሪካዊ ስፍራዎችን በአረንጓዴ መሸፈን ለስነ ምህዳር መሻሻል ሚናው የጎላ ነው--የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) በአረንጓዴ አሻራው መርሐ ግብር ታሪካዊ ስፍራዎችን በአረንጓዴ መሸፈን ለስነ ምህዳር ጥበቃ ሚናው የጎላ እንደሆነ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ተናገሩ።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በታወጀው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁሉም ተቋማት በየፊናቸው አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ።

በአንዳንድ ሥፍራዎች የነብሩ አረንጓዴ አሻራዎች ደግሞ መልከ ብዙ ፋይዳ ያላቸውና ቀልብን የሚገዙም ናቸው።

ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ የአያሌ ታሪካዊ ተስፋዎችና ቅርሶች ባለቤቷ ሆኗ ዳሩ ሐመልማላዊ ገጽታ የተነፈጉ የቱሪዝም ጸጋዎቿን በአረንጓዴ ካባ የማልበስ እሳቤ ነው።

የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል አመራርና ሠራተኞች በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚያሳርፉባቸው ስፍራዎች ታሪካዊ ቅርሶችና ስፍራዎች ናቸው።

ከነዚህም መካከል ቀደም ሲል በመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ፣ በጢያ ትክል ድንጋይ፣ በቅዱስ ላልይበላ ታሪካዊ ስፍራዎችና በወንጪ ሐይቅ መሰህቦች አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን፤ ከሰሞኑም በአንጎለላ ታሪካዊ ስፍራ አገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል።

የሸዋው ንጉሥ ሳሕለስላሴ ወሰንሠገድ ደማቅ ከተማ እንደነበረች የሚነገርላት አንጎለላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪካዊ ቅርሶች እየታደሱ፣ ስፍራውም ወደ አዲስ ከተማነት እየተለወጠ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊቷ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን፣ የፊታውራሪ ገበየሁ አጽምና በአቅራቢያ ከሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ የትውልድ ስፋራ(እንቁላል ኮሶ) መገኘቱ አካባቢው ለቱሪዝም መዳረሻነት ያለው ፋይዳም አሳድጎታል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግም የማዕከሉ ሠራተኞች ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ጋር በመሆን በእነኚህ ታሪካዊ ስፍራዎች ነው አሻራዎችን ያሳረፉት።

የማዕከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ የቱሪዝም ጉዳይ የሚመሩት የስልጠና ተቋም ሕልውና መሰረት እንደሆነ ገልጸው፤ ታሪካዊ ስፍራዎች ችግኝ መትከል የሚሰጠው ስሜትና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳ ከፍተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ማዕከሉ በተያዘው ዓመት 5 ሺህ ችግኞችን በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ለመትከል ያቀዱ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ3 ሺህ በላይ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።

በአንጎለላ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት እንደተከሏቸው የሚነገርላችው ሁለት የኮርችና የሾላ ዛፎች ይገኛሉ።

በተለይም የኮርች ዛፉ ለመብረቅ መከላከያ ተብሎ እንደተተከለ የሚነገር ሲሆን፤ በዚህ ስፍራ ሌላ ችግኝ መትከል የሚሰጠው ስሜትም ከፍተኛ እንደሆነ አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ።

ዛፍ ተፈጥሯዊ አደጋን በተፈጥሯዊ መፍትሔ የመከላከል እሴት ማሳያ እንደሆነ ገልጸው፤ አገር በቀል ችግኞችን መትከል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ለማህበራዊና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ አገር በቀል እዕዋት ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።

አስተያይታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የማዕከሉ መምህራንም በታሪካዊ ስፍራዎች አረንጓዴ አሻራዎችን ማሳረፍ ለስነ ምህዳራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላሉ።

በታሪካዊ ስፍራዎች ታሪካዊ አሻራን በማሳረፍ ሁለም ሰው መሳተፍ ያለበት ተግባር ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም