ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሊት በስኬት በመጠናቀቁ ደስታውን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16/2012 ( ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሊት በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል።

"የሕዳሴው ግድብ ባለቤቶች እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን" ያለው ፓርቲው ኢትዮጵያ በታታሪና ቆራጥ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ በዓለም ፊት ደምቃ የታየችበት የድል ቀን ነው ብሏል።

በግንባታው የአገር መሪዎች፣ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፣ የትምህርትና የእምነት ተቋማት፣ በአጠቃላይ ሁሉም ዜጎች ደማቅ አሻራቸውን አሳርፈውበታል።

በጉባ በረሃ ሌት ተቀን የሚሰሩ ባለሙያዎችና የሠራዊት አባላት በየዕለቱ ታሪክ ፅፈውበታል ሲልም አክሏል።

የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ የየራሳቸውን አሻራ ያሳረፉበት እንደመሆኑ የመጀመሪያው ዓመት የውሃ ሙሊት በስኬት መጠናቀቅ "ሁላችንም ብሔራዊ ኩራት እንድንጎናፀፍ ያስቻለን የድል ብስራት ነው" ብሏል።

ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ክብርና ጥቅም የማይደራደር፤ የኢትዮጵያ ራዕይ እውን የሚሆነው በብልፅግና መንገድ ብቻ እንደሆነ በፅናት የሚያምንና ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚተጋ በመሆኑ በተገኘው ስኬት እንኮራለን ብሏል።

ይህን ድል ጠብቀን ሌሎች ብዙ ድሎችን ለማስመዝገብ እንደምንተጋም በዚሁ አጋጣሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቃላችንን እናድሳለን ብሏል ለኢዜአ በላከው መግለጫ።

አንደ ፓርቲው መግለጫ በአገሪቷ የተመዘገበው ለውጥ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስም እጅግ አስፈላጊና የሚቻልም እንደሆነ በበርካታ ማሳያዎች እያረጋገጠ መጥቷል።

የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሊት ከታሰበው ጊዜ በፊት ቀድሞ መጠናቀቁም የዚሁ አንዱ ማረጋገጫ ነው ይላል መግለጫው።

የዛሬው ድላችን በቀሪ የግንባታ ስራዎችም እንድንበረታ የሚያነሳሳን፣ በዲፕሎማሲ መስክም ይበልጥ ተደማጭ እንድንሆን ጉልበት የሚሰጠን አቢይ ስኬት እንጂ ለአፍታም የምንዘናጋበት ሊሆን አይገባውም።

"ዛሬ የደረስንበት የግንባታ ደረጃና የውሃ ሙሊት የግድቡን ግንባታ ከጀመርን ወዲህ በመስኩ ከታዩ አንኳር ስኬቶች ተርታ የሚሰለፍ ቢሆንም አገራችንን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር የምናደርገው ጉዞ በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደትናንቱ ለሀገራችሁ ብልፅግና ሁለንተናዊ ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በከፍተኛ አክብሮት እንጠይቃለን" ሲልም ጥሪውን አቅርቧል። 

በአባይ ወንዝ ላይ የሰራነው ግድብ ለእኛ የብልፅግናችን ሁነኛ መሰረት ሆኖ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እንድናቅድና እንድንፈፅም የሞራል ስንቅና የፋይናንስ ምንጭ የሚሆነን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ቢሆንም ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ደግሞ በመተባበርና በመከባበር ላይ ለተመሰረተ የጋራ እድገት መታሰቢያ እንዲሆን በሌለ አቅማችን ያበረከትነው ስጦታ ነውም ብሏል።

ከሕዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣል ጀምሮ የአባይ ውሃን የፍሰት አቅጣጫ ለመቀየር እንዲሁም አሁን የውሃውን ያልተገደበ የፍሰት ሁኔታ በፈለግነው መጠን ለመቆጣጠር መቻላችን በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የተመሰረተ አድሏዊ አሰራር የመሸበት፤ በአንፃሩ በጋራ ተጠቃሚነትና በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ ቀጠናዊ ትስስር ብሩህ ንጋት የፈነጠቀበት ሂደት እንደሆነም ገልጿል።

የውሃ አሞላል ሂደቱ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር መፈፀሙ በራሱ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በአንድነት የመበልፀግ ዓላማ እንጂ የትኛውንም አገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በተጨባጭ ያሳየ መሆኑንም ጠቅሷል።

እኛ በላያችን ላይ የተጫነውን የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም አሽቀንጥረን እስከምንጥል፣ የሕዳሴ ግድባችን ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እስከሚጀምር ድረስ ዓይናችንን ለአፍታም ከግድቡ ላይ አንነቅልም" ብሏል ብልፅግና ፓርቲ።

የእስካሁኑ ስኬት ከኋላ እየተከተሉ ለሚጎትቱንና ከፊት እየቀደሙ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎች የክፋት ሴራቸው መቼም እንደማይሳካና የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸው የከሸፈ መሆኑን የሚረዱበት ዕድል የሰጣቸው መሆኑን እናምናለን ብሏል።

"ኢትዮጵያዊያን "እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!!" ብለን ከዘጠኝ ዓመት በፊት ቆርጠን የተነሳንበትን ይህን ብሔራዊ ፕሮጀክት በፈተናዎች ውጣ ውረድ ሳንበገር ይኸው ደግሞ "እንደጀመርነው ጨርሰንዋል!!" ብለን ለመዘመር ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶናል" ይላል የፓርቲው መግለጫ።

"እንደ መሪ ፓርቲ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከታዩ ስህተቶች ተምረን፣ የሕዝባችንን እምነት ሳናጓድል የግድቡን ግንባታ ከዳር እናደርሰዋለን፤ ለዚህም የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግታችሁ እንድትሰሩ፣ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ከጎናችን እንድትቆሙ" ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

ይህ ትውልድ የአያት ቅድመ አያቶቹን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቹ የሚተላለፍ ህያው ታሪክ ሰርቶ ማለፍ እንደሚችል የሕዳሴው ግድብ ህያው ምልክት ነው በማለትም ስኬቱን አሳይቷል።

"ለዓመታት የደከማችሁበት ግድብ ተጠናቆ ፍሬውን እስከምናይ መላ ኢትዮጵያዊያን የመንግስት ተቋማትን መመሪያና የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር በመከተል ራሳችሁን ከኮሮና ወረርሽኝ እንድትጠብቁ ብልፅግና ፓርቲ አደራ ለማለት ይወዳል" ሲልም መልዕክቱን ቋጭቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም