በጎንደር ከተማ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች የተገኘበት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች የተገኘበት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ
ጎንደር፣ ሐምሌ 16/2012 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በመኖሪያ ቤቱ ተገኝቶበታል የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው የሰላምና የህዝብ ደህንነት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አንደበት ከበደ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው በጎንደር ማራኪ ክፍለ ከተማ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የተደበቀ የጦር መሳሪያዎች ተገኝቶበት ነው።
ከግለሰቡ መኖሪያ ቤት ከተገኙት የጦር መሳሪያዎች መካከል አምስት ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች እና ሁለት ሽጉጦች ይገኙበታል፡፡
የከተማው የጸጥታ ኃይል ከህብረተሰቡ በደረሳቸው ጥቆማ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ማግኘት መቻሉን አቶ አንደበት ተናግረዋል፡፡
በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስራ የዋለው ግለሰብ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በከተማው ቀበሌ 18 ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በድብቅ በተሸከርካሪ ሲንቀሳቀስ የነበረ 7 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ በቀጥጥር ስር መዋሉን የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ጨምረው ገልጸዋል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዝ የተገኘው ተሸከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ሾፌሩ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም አመልክተዋል።