ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፈንድ ለማቋቋም ውይይት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፈንድ ለማቋቋም ውይይት ጀመሩ
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ፈንድ ማቋቋም የሚያስችላቸውን ውይይት ጀመሩ። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግላጫ ሶስቱን አገራት የሚያስተሳስር የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመለየት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ውይይቱ የሶስቱ አገራት መሪዎች ከ30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ጎንለጎን አገራቱ በጋራ የሚጠቀሙባቸው የልማትና ኢንቨስትመንት ፕሮጀቶችን ፋይናንስ የሚደግፍ ፈንድ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህም የሶስቱ አገራት ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ፕሮጀክቶችን በገንዘብ የሚደግፍ የጋራ ፈንድ ለማቋቋም ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2010 ዓ.ም በግብፅ ርዕሰ መዲና ካይሮ የመጀመሪያ ውይይት አድርገዋል። አገራቱ በመሰረተ ልማት የሚያስተሳስሯቸውንና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ፕሮጀክሮች የለዩ ሲሆን የጋራ ፈንዱን የሚያስተዳድሩ የኮሚቴዎች አወቃቀርና ይዘት ዙሪያ ምክክር ተደርጓል። በጋራ ፈንዱ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ የህግ አማካሪዎች ቡድን ወደ ስራ ለማስገባት መስማማታቸውንና ለፈንዱ ፈሰስ በሚደረገው የፋይናንስ መጠን፣ ምንነትና ምንጮች ዙሪያም ውይይት ማድረጋቸውን መግለጫው አስታውቋል። የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችም የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንና ሌሎች አገራትም በሶስቱ አገራት ግብዣ አማካኝነት ወደ ጋራ ፈንዱ ሊቀላቀሉ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል። የሶስቱ አገሮች ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ሁለተኛ ዙር ስብሰባ በሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።