ቀጥታ፡

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ እድገት የሚያመጣ ወሳኝ ምዕራፍ ነው - ምሁራን

አዳማ ሐምሌ 15/2012 (ኢዜአ ) የህዳሴው ግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ የስልጣኔና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የሚያመጣ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት የግድቡ ቀሪ ግንባታ  ተጠናቆ  የተሟላ አገልገሎት እንዲጀምር እያንዳንዱ ዜጋ ተቀናጅቶና ተባብሮ መደገፍ ይጠበቅበታል።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ መምህር ዶክተር አሰፋ አባሁምና  የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያንን በጨለማ የኖረበት  ታሪክ እንዲያበቃ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው።

መገናኛ ብዙሃን ከሌሎች የልማት ተግባራት በተጓዳኝ በግድቡ መገንባት ስለሚያስገኘው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እውነታውን ለውጪው ዓለም ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል።

ግብጽና ሱዳንም ይኸንን ተገንዝበው በአረንጓዴ አሻራና በሌሎችም የግድቡ የልማት ስራዎች ላይ ቢያግዙ ጥሩ እንደነበር ያወሱት ዶክተር አሰፋ፤ አሁንም ኢትዮጵያዊያን ከመንግስት በመተባባር ከግብ ማድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የአድዋ ድል ታሪክ ራሱን የደገመበት መሆኑንን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃና የኢንቫይሮንሜንታል ምህንድስና መምህር ዶክተር ኬይረዲን ተማም ናቸው።

ከውጭና ውስጥ  የሚነሱ አፍራሽ  ዘመቻዎችን ወደ ጎን በመተው ግድቡ ዛሬ የመጀመሪያው የውሃው ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ  ለውሸታሞች ትክክለኛ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ አሁን ከደረሰበት ፈጥኖ ቀሪዎቹ ስራዎች  ተጠናቀው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር እያንዳንዱ ዜጋ ተቀናጅቶና ተባብሮ መደገፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የአሁኑ የውሃ ሙሌት ለነበርንበት ቁጭት በራሳችን ምላሽ ያገኘንበት ነው ያሉት ዶክተር ኬይረዲን፤ ይኸ ስኬት የመጨረሻው ባለመሆኑ  የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ዲን ዶክተር ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ በበኩላቸው  የአሁኑ የውሃ ሙሌት ሀገሪቱ  በራሷ እቅድ ተመርታ እንደምትፈጽም ያሳየ ነው ብለዋል።

ይህ  ስኬት ለህዝብና ለሀገር ሉዓላዊነት  ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በግድቡ ዙሪያ ሲነሱ ለነበሩ ፕሮፖጋንዳዎች በቂ ምላሽ የተሰጠበትና ማስተማሪያ የሆነ የተሳካ ክንውን መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ግድቡን ጨምሮ  ሌሎች የሀገር ህልውናን የሚያስጠብቁ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ ከህዝብ ጋር በትብብር መስራት አለበት ብለዋል።

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያ  ወደ ከፍተኛ የስልጣኔና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ማማ ለመውጣት ጭምር ወሳኝ ምዕራፍ  መሆኑን ምሁራን ተናግረዋል።

ይህም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ  በማኩራት እንዳስደሰተ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም