የግድቡ ውኃ ሙሌት መካሔድ የህወሓትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያከሸፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ውኃ ሙሌት መካሔድ የህወሓትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያከሸፈ ነው
አሶሳ፤ሐምሌ 15 / 2012 (ኢዜአ) የህዳሴው ግድብ ውኃ ሙሌት ህወሓት በፕሮጀክቱ ላይ የሚነዛውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ያከሸፈ ነው ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለፁ ።
ርእሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት ላይ በመድረሱ መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል ።
ግድቡ ባጋጠሙት ችግሮች ግንባታው መዘግየቱን ያስታወሱት አቶ አሻድሊ የውኃ ሙሌት እንዲጀመር የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያ ህዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ወስጥ የወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል ።
በተለይም በህወሓት በኩል በግድቡ ላይ ሲነዙ የነበሩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ያከሸፈ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ ፕሮጀክቱ በዚህ ወቅት ለውኃ ሙሌት እንደማይደርስ በእርግጠኝነት መናገር እንደሚቻልም ርእሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል ።
የግድቡ ውኃ ሙሌት መከናወኑ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታላቅ መነቃቃትና ተስፋ መፍጠሩንም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።
በሀሰት ፕሮፖጋንዳው የተታለሉ ግለሰቦችን ግድቡ ተሽጧል የሚለውን ወሬ የከሸፈ መሆኑን በመረዳት ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ርእሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ።
የጊዜ ጉዳይ እንጂ በለውጡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ እየተጠናቀቁ የሀገራችን ብልፅግና የሚፋጠንበትና የለውጥ አደናቃፊዎች ደግሞ ወደ ኋላ የሚቀሩበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለዋል ።
ግድቡ የኢትዮጵያዊያንን ህዳሴ ለማፋጠን እንጂ ሌሎችን ለመጉዳት እንዳልሆነ የተፋሰሱ ሀገራትም ሊረዱት ይገባል ብለዋል ።
መላው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ርእሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ።