የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያዊያን የጥንቱን ገናና ስልጣኔ እያስቀጠሉ ስለመሆኑ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያዊያን የጥንቱን ገናና ስልጣኔ እያስቀጠሉ ስለመሆኑ ማሳያ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 15/2012 የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያዊያን የጥንቱን ገናና ስልጣኔ እያስቀጠሉ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ መሆኑ ተገለጸ።
በተለያየ ሰበብ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ አስተዋፅኦ ያላደረገ ኢትዮጵያዊ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚሰማው ጸጸት ከባድ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
በእዚህ ወቅትም የግድቡ ግንባታ ሥራ ከመጠናቀቁ በፊት ሁሉም ሰው ለዓባይ ግድብ የታሪክ አሻራውን ማስቀመጥ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሕዳሴው ግድብ እንደ ላልይበላ፣ ጀጎል፣ አልነጃሽ፣ አክሱምና ሌሎች የጥንት የኢትዮጵያ ስልጣኔ መገለጫዎች ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ወደፊት የሚሚሰገንበትና የሚወሳበት ታሪክ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በእዚህ ወቅት እንዳሉት የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ የ700 ዓመት ጥያቄና የቀጣይ ትውልድ መመኪያ ነው።
"ኢትዮጵያዊያን ጥንት የዓለም ስልጣኔ ሳይጀምር ስልጣኔን ያስተማሩ መሆናቸውንና አሁንም በዚያ የስልጣኔ ጎዳና እየተጓዙ መሆናቸውን ግድቡ አንድ ማሳያም ነው" ብለዋል።
በግድቡ ግንባታ ላይ መሳተፍ ቀጣይ የሚወለደው ልጅ የኔም አባት በዚህ ሥራ ላይ አሻራው አለበት ብሎ እንዲኮራ ያደርጋል፤ አለመሳተፍ ደግሞ ለማይሽር ፀፀት እንደሚዳርግ ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ሥራ ለመጠናቀቅ መቃረቡ ደግሞ ሁሉም ሰው በሞራል እንዲሳተፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያዊያን በቀጣይም ከዚህ የበለጠ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑንና ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ አንድነቱንና አገራዊ ስሜቱን ይዞ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።