የክልል ሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ሞተርሳይክሎች በአዲስ አባበ እንዳይንቀሳቀሱ ታገደ - ኢዜአ አማርኛ
የክልል ሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ሞተርሳይክሎች በአዲስ አባበ እንዳይንቀሳቀሱ ታገደ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 15/2012 የክልል ሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ሞተርሳይክሎች ለወንጀል መበራከት ምክንያት እየሆኑ በመምጣታቸው በከተማው እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ስጥቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ስጦታው አካለ እንዳሉት በከተማው ለወንጀል መበራከትና ለትራፊክ ፍሰቱ ተግዳሮት እየሆኑ የመጡ የክልል ሰሌዳ ቁጥር ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ሞተር ሳይክሎች እገዳ ተጥሎባቸዋል።
"እነዚህ ሞተር ሳይክሎች ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ በህግ ይጠየቃሉ" ብለዋል።
በከተማው ባለፉት ሁለት ዓመታት ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ከትናንሽ እስከ ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጸምባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።
ባለቤታቸው የማይታወቅና ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች በከተማዋ መበራከት ለትራፊክ አደጋና ፍሰትም ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አቶ ስጦታው እንዳሉት የከተማው አስተዳደር ይህንን ችግር ለመፍታት ባለፈው ዓመት አስገዳጅ መመሪያን ተግባራዊ አድርጓል።
በዚህም ሳቢያ በከተማው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት 15 ሺህ ሞተር ሳይክሎች መካከል ህጋዊ የሆኑት 3 ሺህ 600 ሞተር ሳይክሎች በ56 ማህበራት ተደራጅተው ህጋዊ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን ነው የጠቆሙት።
እስካሁን ድረስ በከተማው እንዲንቀሳቀሱ ፈቃድ ካገኙት ሞተርሳይክሎች ውጪ በቀጣይ ምንም ዓይነት ፈቃድ እንደማይሰጥ አቶ ስጦታው ተናግረዋል።
ለዚህ ውሳኔም በከተማው ያለው የትራፊክ ፍሰት መብዛት ተጨማሪ ሞተርሳይክሎችን ለማስተናገድ አለመቻሉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም "በቅርቡ በተደረገው የማጣራት ሥራ የክልል ሰለዴ ቁጥር ለጥፈው በከተማው ወንጀል ሲሰሩ የተገኙ ሞተር ሳይክሎች መበራከት እገዳው እንዲጣል አስገድዷል" ብለዋል።
የሞተር አሽከርካሪዎች ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ከተደረገ በኋላ በእነሱ የሚፈጸም ወንጀል መቀነሱንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለማቀፍ ደረጃ ከሚደርሱ አጠቃላይ የትራፊክ አደጋዎች 20 በመቶው የሚሆኑት በሞተር ሳይክል የሚፈጸሙ ናቸው።