በባህር ዳር ከተማ የተቋቋመ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ማምረት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ የተቋቋመ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ማምረት ጀመረ
ባህር ዳር ኢዜአ ሐምሌ 14/2012 በባህር ዳር ከተማ 410 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተቋቋመ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ ማምረት ጀመረ።
የዘይት ፋብሪካው በቀን 21 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው በምረቃው ስነስርዓት ወቅት ተገልጿል።
በስነስርዓቱ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ውጣ ውረድ የሚጠይቁ ስራዎችን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነና ታታሪ የሰው ኃይል ያለበት አካባቢ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት መልማት የሚጠበቅበትን ያህል ሳይሆን መቆየቱን አውስተዋል።
በአካባቢው አልፎ አልፎ ይከሰት የነበረው የሰላም መደፍረስ፣ ለፋብሪካዎች መስፋፋት አስፈለጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች አለመስፋፋት ኢንቨስትመንቱን ጎድቶት ቆይቷል ብለዋል።
አሁን በአንድ በኩል የክልሉን ሰላም በማስከበር በሌላ በኩል ደግሞ ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ መሰረተ ልማቶችን የማሟላትና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ አቅም መፈታት የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሙሉነሽ በፌዴራል መንግስት የሚፈቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረቶችን ለማሰተካከልም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህዝቡ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ሰላሙን በማስጠበቅ ረገድ ከመንግስት ጎን እንዲቆም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ በበኩላቸው መዋለ ንዋያቸውን በክልሉ ለመፍሰስ ለሚመጡ ባለሀብቶች መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ለዘመናት በማጠር የሚያቆዩ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የወሰዱትን መሬት አጥረው ባስቀመጡና ከታቀደለት ዓላማ ውጪ እያዋሉ ያሉ የክልሉ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
የባህር ዳር ከተማን ከቱሪዝም መዳረሻነት ባለፈ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ፋብሪካው 410 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በዘጠኝ ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተቋቋመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቶብ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ጌታሰው አያሌው ናቸው።
አሁን ላይ ለ180 ሰራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው የፋብሪካው ዓላማ ትርፍ መሰብሰብ ሳይሆን የስራ እድል በመፍጠርና እንደ ሀገር እጥረት የሆነውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ለማገዝ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ፋብሪካውን ለማቋቋም ላደረገላቸው ቀና ትብብርም አመስግነዋል።
በምረቃው ስነስርዓት የክልሉ መንግስት ስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።