ቀጥታ፡

በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ውድመት በተማሪዎች ላይ የስነ-ልቦና ጉዳት አድርሷል - መምህራንና ወላጆች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 14/2012 ( ኢዜአ) በሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከት ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ውድመት በተማሪዎች ላይ የስነ-ልቦና ጉዳት ማድረሱን መምህራንና ወላጆች ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ወላጆች ልጆቻቸው እውቀት የሚቀስሙባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ በደረሰው ውድመት ማዘናቸውንም ገልፀዋል።

በአርሲ ነገሌና በሻሸመኔ ከተሞች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ከወደሙ ተቋማት መካከል ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።

በአርሲ ነገሌ ከተማ የሚገኘው የጭላሎ 1ኛ ደረጃ እና በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው የሉሲ 2ኛ ትምህርት ቤቶች በግርግሩ የእሣት ሰለባ ሆነዋል።   

ተማሪዎች ለዓመታት የደከሙበት የትምህርት ማስረጃም በእሣት ተቃጥሏል።

የሉሲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዘሪሁን ደመቀ እንደገለጹት  አገር ተረካቢ  ትውልድ በሚያፈራው የትምህርት ተቋም ላይ የደረሰው ጉዳት አሳዛኝ ነው።

በትምህርት ቤቱ የሚገኝ የተማሪዎች የትምህርት ማስረጃና መረጃ መውደሙንም ተናግረዋል።

በአርሲ ነገሌ ከተማ የጭላሎ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አብዲ ዋቤ በበኩላቸው ጥያቄ ያለው አካል በሠላማዊ መንገድ ማቅረብ እንጂ ንብረት ማውደም የማይገባ ተግባር ነው ብለዋል።

እየተስተዋለ ያለው በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳት ከመስመር የወጣ  እንደሆነም ተናግረዋል።

ትምህርት ቤት የአንድ ግለሰብ ብቻ አይደልም ያሉት መምህር ዘሪሁንም በትምህርት  ቤቱ ላይ በደረሰው ጉዳት የ350 ሠራተኞች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ ላይ የደረሰው ውድመት የመምህራን፣ የማኅበረሰቡንና  የተማሪዎችንም  ስሜት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርበታል ያሉት መምህሩ ትዕግስትም ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረውም አመልክተዋል።

የተማሪዎች ወላጆችም ልጆቻቸው እውቀት የሚቀስሙባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ በደረሰው ውድመት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የሁሉም ኅብረተሰብ ሃብት በሆኑት ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ውድመት በልጆቻቸው አዕምሮ ላይ ጫና ማሳደሩንና የስነ-ልቦና ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም