ድርጅቱ ለ50 ሴት የጎዳና ተዳዳሪዎችና ልጆቻቸው ለአንድ ወር ማዕድ ማጋራት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ ለ50 ሴት የጎዳና ተዳዳሪዎችና ልጆቻቸው ለአንድ ወር ማዕድ ማጋራት ጀመረ
ሐምሌ 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ለ50 ሴት የጎዳና ተዳዳሪዎችና ልጆቻቸው ለአንድ ወር የሚቆይ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አስጀምሯል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አርአያስላሴ ተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው ተግባራት አንዱ የሆነውን የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ማስጀመሩን ገልጸዋል።
በአንድ ወር የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ሴቶቹና ልጆቻቸው በፍልውሃ ሆቴሎች ድርጅት ምሳ የሚመገቡ ሲሆን ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ድርጅቱ ለማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ 110 ሺህ ብር በመመደብ በተለይ እናቶችና ሕፃናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።
ወጪው በዚህ ዓመት ካገኘው የትርፍ ገቢ ላይ የተመደበ ሲሆን በቀጣይም በሠራተኞች መዋጮ ጭምር ተመሳሳይ ተግባራትን በቋሚነት ለመከወን መታቀዱን ጠቁመዋል።
የማዕድ ማጋራቱ ተጠቃሚዎችም ድጋፉ በተለይ እናቶችና ሕፃናት ልጆቻቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከተመሰረተ 126 ዓመታትን አስቆጥሯል።