በጌዴኦ ዞን 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተከፋፈለ - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተከፋፈለ
ዲላ፣ ሐምሌ 14/2012 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለስምንት ወረዳዎች እንዲከፋፈል ማድረጉን የዞኑ ኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ገለፀ ።
የዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ግብረ ሀይል የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከባዱ ወራሳ እንዳሉት በዞኑ ከተለያዩ አካላት ከተሰባሰበው 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ዛሬ ለ8 ወረዳዎችና 4 ከተማ አስተዳደሮች 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ተሰራጭቷል ።
ከተከፋፈሉት ቁሳቁሶች መካከል የጤፍና ፉርኖ ዱቄት ፣አተርና ምስር ፣ፓስታና ማካሮኒ ፣ዘይትና መሰል ምግብ ነክ ድጋፎች ይገኙበታል ።
የንፅህና መጠበቂያ፣ አልባሳትና ጫማዎችም የድጋፉ አካል ናቸው ተብሏል ።
የጌዴኦ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ቡኔ በበኩላቸው በዞኑ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ሊዳረጉ የሚችሉ 123 ሺህ 105 ሰዎች የመለየት ስራ ተከናውኗል ።
ለእነዚህ ወገኖችም የዞኑ የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ሃይል ካሰባሰበው ሃብት መጠባበቂያ በማስቀረት 1 ሺህ 824 ኩንታል ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች መከፋፈሉን አስረድተዋል ።
የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት በማገዙ ረገድ ህብረተሰቡ ፣ ባለሀብቱና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያከናወኑት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በግብረ ኃይሉ የተሰበሰበውን ሐብት የተረከቡት የወረዳና የከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ድጋፉን ለሚመለከታቸው አካላት በተገቢው መንገድ እንዲያሰራጩ አሳስበዋል።