ቀጥታ፡

የቡና ግብይትን በዘመናዊ አሰራር ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2012(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቡና አምራቹን ከተጠቃሚው የሚያስተሳስር ዘመናዊ አሰራር ለማበልጸግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ተስማማ።

የመግባቢያ ሰነዱን  የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የዲጂታል ፕላትፎርምን በማበልጸግ የቡና ምርት ተወዳዳሪነትን ማበረታታትና ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚዘረጋው ዘመናዊ አሰራር አርሶ አደሩን ከተጠቃሚው ጋር ቀጥታ የሚያገናኝና የግብይት ሰንሰለቱን የሚያሳጥር ነው።

ከቀላል የስልክ መተግበሪያዎች ጀምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በቡና ግብይት ስርአቱ ውስጥ እንደሚዘረጋ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የሚበለጽገው ቴክኖሎጂ የቡና አመራረት ሂደት፣ ቦታ፣ አምራች እንዲሁም የአዘገጃጀት ሂደቱን ለገዥዎች ግልጽ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ የተሸጠበትን ዋጋ ከመከታተል ጀምሮ ወደ ተጠቃሚው የሚደርስበትን ጊዜ መከታተል ያስችለዋል ተብሏል።

ለዚህም አርሶ አደሩ በሚረዳው ቋንቋና ቀላል የሆኑ የስልክ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥበትና የሚያገኝበት አሰራር ይዘረጋል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን እንዳሉት፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ ቡና ከሚያቀርቡ አገሮች ጋር እንድትወዳደር አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

አሰራሩን በሌሎች የግብርና ምርቶች ግብይት ላይ መተግበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው የዲጂታል ስትራቴጂ አንደኛው አላማ የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ አሰራር በመደገፍ ምርታማነቱን መጨመር እንደሆነ አንስተዋል።

የቡና ምርትን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ግብይትን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፤ ''በቀጣይ ሌሎች የግብርና ምርቶችን ግብይት የማዘመን ስራ ይጀመራል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብትሆንም ለአለም ገበያ እያቀረበች ያለው ከሶስት በመቶ በታች መሆኑን አውስተዋል።

ለዚህም የግብይት ስርአቱ አለመዘመንና አርሶ አደሩ ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆን ምርቱ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ገበያ እንዳይመጣ ማድረጉን ገልጸዋል።

''የተደረገው ስምምነት የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ ነው'' ብለዋል።

አሰራሩ በገዢና አምራች መካከል መተማመንን በመፍጠር የተሻለ ምርት ለገበያ በማቅረብ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚረዳ ጨምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም