የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል ... የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል ... የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2012 (ኢዜአ) የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ የአገርን ሠላምና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ መገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሕልፈት ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በተነሳ ሁከት ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ በርካታ ንብረትም ወድሟል።
ክስተቱን ሁሉም የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን በሚባል ደረጃ በስፋት ሲዘግቡትም ተስተውሏል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት መገናኛ ብዙኃኑ ለዓመታት ከነበሩበት ጫና ወጥተው በነጻነት እንዲዘግቡና የሕዝቡን ሐሳብ እንዲያስተላልፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይሁን እንጂ ነጻነቱ በአግባቡ የማይጠቀሙና የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር የሚጥሱ መገናኛ ብዙኃን መፈጠራቸውን ጠቁመው፤
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ሽፋን በማድረግ የዜጎችን ሠላምና አብሮነት የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩ ኦ.ኤም.ኤን እና ድምፀ ወያኔ ጣቢያዎች መታገዳቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያም ስርጭቱ እንዲቋረጥ በማድረግ በመንግስት እርምጃ እንደተወሰደበት አስታውሰዋል።
መንግሥት ሠላም ለማስከበር ከወሰደው እርምጃ ጎን ለጎን መገናኛ ብዙኃኑን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ባለሥልጣኑ አዋጁ በሚፈቅድለት ሕግና ደንብ መሠረት ኃላፊነቱን የሚወጣበትና የማይታገስበት ጊዜ መሆኑን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃን ድንጋይ መወራወሪያ ሳይሆን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦች የሚፋጩባቸውና ሃሳብ የሚያሸንፍባቸው ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።
ሕዝቡ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ ይልቅ መቃቃርን የሚሰብኩ የመገናኛ ብዙኃን አሁንም መኖራቸውን አቶ ወንድወሰን አንስተዋል።
የአንድ ወገንና ቡድንን ፍላጎት በሚያንጸባርቁና የተቋቋሙበትን ዓላማ በሚዘነጉ መገናኛ ብዙኃን ላይ አሁንም የእርምት እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የችግራቸው መጠን ቢለያይም የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል የመሆን አዝማሚያ በመገናኛ ብዙኃኑ እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል።
ይህንን ከመሠረቱ ለማስቀረት ባለሥልጣኑ ሕግን በማስከበር መገናኛ ብዙኃኑ ኃላፊነታቸውን በትክክለኛ መንገድ እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 72 የማኅበረሰብ፣ የግል /የንግድ/ እና የሕዝብ ራዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም 37 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ።