በአዲሱ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ? - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ምን ይላሉ?
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን በአዲስ መልክ መጀመራቸው ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ባለፈ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስሩን እንደሚያጠናክር ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ አስመራ በተገኙበት ወቅት ኤርትራውያን ያደረጉላቸው የሞቀ አቀባባል በሁለቱ ህዝቦች መካካል ያለው የሰላም፣ የፍቅርና በጋራ የመስራት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ያሳየ ነው። ለዓመታት የተቋረጠው የኢትዮያና ኤርትራ ግንኙነት መቀጠሉ የሁለቱንም ሀገራት ልማት የሚያፋጥን መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ወጣት ታምራት በቀለ ይናገራል። "በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት የተጀመረው የፍቅርና የመደመር ግንኙነት ታሪካዊ ክስተት ነው" የሚለው ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት እማዋይህ ወንደሰን ነው። "ግንኙነቱ ከሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አልፎ ለቀጠናው ሰላም፣ መረጋጋትና ለጋራ ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው" ሲል ነው ወጣት እማዋይህ የተናገረው። አክሎም ይህ በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን የሰላም ጉዞ ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማስቀጠልና ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች በጋራ በመስራት ለዓለም ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት ዘላቂ እንዲሆን የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ከሁሉም ጋር በመደመር መስራት የግድ መሆኑንም አስምረውበታል። በወንድማማች ህዝቦች መካካል አንድነትና ፍቅር ወደቀድሞው ሁኔታ በመመለሱ የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ወጣት ተማም ቃበቶና ወይዘሮ አበርሂት ተክለጽዮን ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት አስመራ ላይ መፈረሙ ይታወሳል። በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 20 ዓመታት የኖሩበት የጦርነት ድባብ ማብቃቱን ይፋ አድርገዋል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ መስመር የተጀመረ ሲሆን በኢትዮጵያና ኤርትራ ለዘመናት ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦች በቀጣይ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል።