የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኃይል እጥረት ወደ ስራ ማስገባት አልተቻለም- ኮርፖሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኃይል እጥረት ወደ ስራ ማስገባት አልተቻለም- ኮርፖሬሽኑ
ባህርዳር፤ሐምሌ 14/ 2012 (ኢዜአ) የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደሴ አሰሜ እንደገለጹት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው።
ፓርኩ በአካባቢው በሰብል፣ እንስሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፎች አርሶ አደሮች ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ትርፍ ማምረት በመጀመራቸው የተፈጠረው የገበያ ክፍተት ለመሙላት ታስቦ የተቋቋመ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ በ260 ሄክታር መሬት ላይ እንደተገነባ አመልክተው የፓርኩን ግንባታ ከ93 በመቶ በላይ ተጠናቆ ለስራ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በፓርኩ ውስጥ የአስተዳደር፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የስልጠናና ምርምር፣ የትምህርት ቤት፣ የመንገድና የውሃ አቅርቦት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የፓርኩ ግንባታ ባለሃብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በሚያስችልበት ደረጃ ላይ ቢገኝም የኤሌክትሪክ "ሳብስቴሽን" ግንባታና የመስመር ዝርጋታ አለመጀመሩ ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሉን አቶ ደሴ አስታውቀዋል።
እስከ አራት ቢሊየን ብር ወጭ የተደረገበት የፓርኩ ግንባታ በኃይል እጥረት ወደ ስራ ባለመግባቱ በአርሶ አደሩ ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በተለይም የኤሌክትሪክ "ሳብስቴሽን" ግንባታው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የሚወስድ በመሆኑ ቀደም ብለው ወደ ፓርኩ የገቡና ማምረት የነበረባቸው ባለሃብቶች ችግር ላይ በመሆናቸው መንግስት አፋጣኝ ምላሽ መሰጠት አለበት ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው በክልሉ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማስተናገድ የመብራት አቅርቦት ዋና ማነቆ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ እንዳመለከቱት የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአርሶ አደሩን ልዩ ልዩ ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት በመለወጥ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ነው።
ፓርኩ የአርሶ አደሩን ምርት በማሰባሰብ፣ በማጣራት፣ በማሸግና በከፊል በመለወጥ በክልሉ ትኩረት የተሰጠውን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር ለማፋጠን እንዲቻል በመገንባት ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ፓርኩ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
አዋጭና ችግር ፈቺ የሆኑ ሌሎች የኃይል አቅርቦት አማራጮች ማመቻቸት ከሚችሉ ጋር የክልሉ መንግስት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግና በአመራረት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት በመፍታት የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ በክልሉ ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ጋር ይሰራል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አሁን ባለው ሀገራዊ የአመራረት ዘይቤ ለፋብሪካዎች ግብዓት ማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ የአካባቢ ጸጋዎችን በጥናት በመለየት የምርጥ ዘር አቅርቦትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለዚህም በስራቸው የሚገኘው የቡሬ ግብርና ኮሌጅ ከባህርዳርና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ለፓርኩ ግብዓት ለማቅረብ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የቡሬ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰሞኑን በክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገብኝቷል።
በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ይሄው ፓርክ ግንባታውም በሶስት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚካሄድ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።