ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ቤተሰቦች የ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ

አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ቤተሰቦች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ1ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ፈጸሙ።

በኮቪድ- 19 ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ ከ400 በላይ ወገኖች የምግብ ፍጆታ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የስፖርት አካላት በጋራ ያዘጋጁት የግድቡ የቦንድ ግዥ፣ የማዕድ ማጋራትና የክረምት በጎ አድራጎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲዬም ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዘመን ጁነዲ ቦንዱን 32ቱ ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ቤተሰቦች መግዛታቸውን ገልጸዋል።

አካላቱ ቦንዱን በመግዛት ላሳዩት መነሳሳትም አድንቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ በዚሁ ጊዜ የግድቡ የውሃ ሙሌት ከጫፍ በደረሰበት በዚህ ወቅት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በኅብረተሰቡ ዘንድ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸው እንዳይቋረጡ አሳስበዋል።

የስፖርት አካላት ኃላፊዎች በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ በበኩላቸው አካላቱ ከቦንድ ግዥው በተጨማሪ በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው 400 ሰዎች የአንድ ወር የምግብ ፍጆታ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ የአረጋውያንን ቤቶችን በማደስ፣አካባቢን በማጽዳትና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ተሳትፎ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም