መንግስት የህዝብን ሰላም በሚያውኩ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የህዝብን ሰላም በሚያውኩ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ
ፍቼ ሐምሌ 13/2012(ኢዜአ) ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ የህዝብን ሰላም በሚያውኩ አካላት ላይ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የደገም ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ።
ነዋሪዎቹ በወቅታዊው የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ በመከሩበት ወቅት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቁ አካላት በወረዳው የተወሰኑ ቀበሌዎች በመንቀሳቀስ በህብረተሰቡ ላይ ዘረፋና ግድያ እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የያያ ሀሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቶሊ ጅማ እንደገለጹት በአካባቢያቸው በህገ-ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ አካላት ምክንያት ተረጋግተው ስራቸውን ማከናውን አልቻሉም።
ችግሩን ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ቢሆንም መንግስት አስፈላጊውን የጸጥታ አካላት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጠጂቱ በዳሳ በበኩላቸው ጥቃት በመሰንዘር ጉዳት እያደረሰባቸው ያለው ይሄው ህገ ወጥ አካል በተለይም በሴቶች ላይ የሚያደርሰው በደል አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት ቋሚ የጸጥታ ኃይል በአካባቢው እንዲመድብ ጠቁመዋል።
የቁንዴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበራ አረዳም ህገ-ወጥ ታጣቂው ከባህልና ስነ-ምግባር ያፈነገጠ ተግባር በመፈጸም ላይ የተሰማራ በመሆኑ መንግስት የተጠናከረ የጸጥታ ኃይል በማሰማራት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ጠይቀው እሳቸውና የአካባቢው ነዋሪም የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የአካባቢውን ሰላም ለማወክ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ህዝቡ ከለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የደገም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌቱ ተፈሪ ናቸው።
ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትም ቀደም ሲል በሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ተደጋጋሚ ጥረት መደረጋቸውንም አመልክተዋል።
የዞኑ ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተሰማ ኛፕ እንደተናገሩት በህገ-ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን አካል አጥርቶ ለማውጣት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ህዝቡን በተሳሳተ አመለካከት በማታለልና የህገ-ወጥ አካሉ ተባባሪ በማድረግ የፀጥታ ኃይሉ ላይ ሳይቀር ጉዳት ሲደርስበት መቆየቱን አውስተዋል።
ህብረተሰቡ ዛሬም ነገም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ሰላሙን ማረጋገጥ እንደሚገባውም ኮማንደሩ አሳስበዋል።
በውይይቱ ወቅት የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንደሻው ብርሃኑ በህገ-ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ የሚንቀሳቀስን ማንኛውንም አካል በመቆጣጠር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጠናከረ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።