ቀጥታ፡

የህዳሴውን ግድብ ከደለል ለመታደግ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም እስታወቀ

ባህር ዳር/ደሴ ሐምሌ 13/2012 (ኢዜአ )በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ ስትራቴጅክ ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም አስታወቀ። 

በክልሉ የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች  አመራሮችና ባለሙያዎች በቤዛዊት ተራራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አከናውነዋል።

በዚህ ወቅት የፎረሙ ሰብሳቢ ዶክተር አባተ ጌታሁን እንደገለጹት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ዓላማ የአፈር መሸርሸርን ለማስቆምና የህዳሴ ግድብን ከደለል መሞላት ለመታደግ  ነው።

ክልሉ የዓባይ ግድብ መነሻና ገባር ወንዞች የሚገኙበት ቦታዎች በተለይም ጉና፣ ጮቄ እና ሌሎች በዓባይ አቅራቢያ በሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ መረ ግብር እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የቤዛዊት ተራራም በዓባይ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ በመሆኑና አፈሩ እየተሸረሸረ ወደ ወንዙ ስለሚገባ  ፎረሙ ይህንን ችግር ለመከላከል ቦታውን መርጦ ችግኝ ለመትከል  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ  ከ550 ሀገር በቀል ችግኝ በዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችና ባለሙያዎች መተከሉን ጠቅሰው  ከዚህ ቀደምም በጉናና ጮቄ ተራራዎች ተመሳሳይ መረ ሃግብር ማከናወናቸውን አመልክተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማርና ምርምር ስራዎች ባለፈ የግዙፉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ችግር ቀድሞ በመገንዘብ መፍትሄው ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ፎረሙም ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ በልህ እየገነቡት የሚገኘውን የህዳሴ ግድብ ከአደጋ ለመታደግ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላው  ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህበረተሰቡ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መረሃ ግብርን ሲያከናውን ችግኝ መተከሉን ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊና የተጠና ሊሆን በሚችል መልኩ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የሰውን አእምሮ ከመገንባት ባለፈ አካባቢ ጥበቃ ላይ እየሰሩት ያለ ስራ አርአያ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂክ የሆነ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ከማካሄድ ባለፈ የኮሮና ቫይረስ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን  ጫና በመገንዘብ የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን በውጫሌ ይስማ ንጉስ ታሪካዊ ቦታ ላይ ከአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ አንድ ሺህ ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አካሄደዋል።

ወጣቶቹ ክታር መሬት ላይ ከ50 ሺህ በላይ የሃገር ውስጥና የውጭ ዝርያ ያለቸው እንደሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ተክለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ወንድይሻል ጥጋቡ ወጣቱ የታሪካዊ ቦታዎች ባለቤት ለመሆን በይስማ ንጉስ ስፍራ ችግኝ መትከል መቻላቸው እንዳስደሰተው ተናግሯል።

ወጣቶቹ ባለፈው ዓመት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ በደረሰበት ስፍራ የችግኝ ተከላ ማከናወናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም