በባህርዳር ከተማ የተገነባው የአልሚ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመረቀ

93

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 13/2012(ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ 214 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው የቋሪት አልሚ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። 
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ አልሚ ባለሃብቶችን በማበረታታት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የፋብሪካው መገንባት በአካባቢው የሚለማውን ጥሬ ምርት በግብዓትነት በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

በክልሉ በቂ ሰብል  የሚመረት ቢሆንም በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ችግር በህፃናት ላይ  የመቀንጨርና መቀጨጭ ችግር እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

ችግሩን ለማቃለልም እንደዚህ ዓይነት  ፋብሪካዎችን በክልሉ በቀጣይ በማስፋፋትም ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው እንዲያድጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዛሬ ለምርቃ የበቃው የቋሪት አልሚ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ምርቱን ከክልሉ አልፎ ለአጎራባች ክልሎች እንዲያቀርብም ይመቻቻል ብለዋል።

ለኢንቨስትመንት የሚሰጥ መሬት አጥረው ለሚያስቀምጡ ባለሃብቶች ሳይሆን አልምተው ራሳቸውንም ሆነ ክልሉን ለመለወጥ ፍላጎቱ ላላቸው ድጋፍ  እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ክልሉን ከድህነት ለማላቀቅ አርሶ አደሩ በስፋት የሚያመርተውን ሰብል እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች እንዲበዙም የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አብራርተዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ በበኩላቸው ክልሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የጥሬ ዕቃ ክምችት እንደሚገኝበት ገልጸዋል።

ለምርቃት የበቃው ፋብሪካም  ስራው የተቃና እንዲሆን ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንደራሱ ሃብት ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል ብለዋል።

ፋብሪካውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብተው ለአገልግሎት ያበቁት መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቋሪት አልሚ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሃብታሙ ታደሰ ናቸው።

በክልሉ በአልሚ ምግብ አቅርቦት እጥረት የሚስተዋለውን የመቀንጨር በሽታ ችግር ለመከላከል አስበው ፋብሪካውን እንደገነቡት ገልጸዋል።

ፋብሪካው በቀን አንድ ሺህ 500 ኩንታል አልሚ ምግብ የማምረት አቅም እንዳለውና  200 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

ባለሀብቱ በቀጣይም የእንስሳት መኖና የሌላም ሰብል  ማቀነባበር የሚያስችሉ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባት አቅደዋል። 

በምረቃው ስነስርዓት ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም