ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 13/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከተቋቋመበት የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አገልግሎት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጿል።

የድርጅት ሰራተኞችና አመራሮች ዛሬ የአረንጓዴ አሻራቸውን ለማኖር በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 1 ሺህ 500 ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም ተክሌ እንደገለጹት፤ የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ከመስጠት ባለፈ በማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ በማድረግ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። 

ድርጅቱ በአገር ዓቀፉ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በመሳተፍ የበኩሉን መወጣቱን ተናግረው፤ የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እስኪበቁ ድረስ የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ድርጅቱ በአረንጓዴ አሻራ ካለው ተሳትፎ በተጨማሪ በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንደሚሳተፍ የገለጹት አቶ ወንድም፤ በደም ልገሳ እና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጫና ለተፈጠረባቸው ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ተሳትፎ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከተቋቋመበት የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አገልግሎት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሰራተኞች በበኩላቸው ዛፍ መትከል ለትውልድ አሻራን የማስተላለፍ ስራ በመሆኑ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።


የአረንጓዴ አሻራ ስራ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑንም አመልክተዋል።

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋይናንስና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሲሳይ አስፋው በበኩላቸው ''ድርጅቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን በፓርኩ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እየተካሄደ ይገኛል'' ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት በፓርኩ ውስጥ ከ28 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት አቶ ሲሳይ፤ ዘንድሮ 143 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

የኢንዱሰትሪ ፓርኩ 354 ሺህ ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30 ሄክታር ያህሉ ለአረንጓዴ ቦታ የተያዘና ዛፍ የሚተከልበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም