የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።
ሚኒስትሯ ዜጎችን ከቫይረሱ በመከላከል ረገድ የጸጥታ መዋቅሩና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል።
ዶክተር ሊያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።
''በትናንናው እለት በአንድ ቀን ብቻ 704 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ደግሞ ለዚህ ማሳያ ነው'' ብለዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ሰዎች በላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንም አስረድተዋል።
አገር አቀፍ የምርመራ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ''ካለን የህዝብ ቁጥር አንጻር የምርመራ አቅማችንን ይበልጥ ለመጨር እንሰራለን'' ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሊያ ገላጻ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ 45 የላቦራቶሪ ማዕከላትን በማቋቋም በቀን እስከ 10 ሺህ የመመርመር አቅም ተፈጥሯል።
በተፈጠረው አቅምም በቀን ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎችን መመርመር መጀመሩን አስረድተዋል።
ቫይረሱን የመከላከያ ዘዴዎች ቀላልና ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቁ በመሆናቸው ማህበረሰቡ አሁንም ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው ሚኒስትሯ ጥሪ ያቀረቡት።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ረገድ መዘናጋቶች እየታዩ መሆኑን አንስተው፤ ህብረተሰቡ ከዚህ አንጻር ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ አባላት ማህበረሰቡ የጥንቃቄ ምክረ ሃሳቦችን እንዲተገብር በመቆጣጠርና ራሳቸውም አርኣያ በመሆን ረገድ እያበረከቱ ላላው አስተዋጽኦም ምስጋናና እውቅና ሰጥተዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላው አገሪቱ ከ18 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት 35 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ማከናወኑንም ተናግረው፤ማህበሩ እያከናወነው ላላው በጎ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።