የሲዳማ ክልልን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ መንግስት አበክሮ ይሰራል- አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልልን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ መንግስት አበክሮ ይሰራል- አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሐዋሳ ሐምሌ 13/2012(ኢዜአ) ሲዳማ ክልልን ለኢንቨስትመንት ተመራጭና መዳረሻ ለማድረግ መንግስት አበክሮ የሚሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደስታ ሌዳሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ጊዜያት ክልል ለመሆን በተደረገው እንቅስቃሴ የተወሰኑ ያልተገቡ ዝንባሌዎችና ተግባራት ነበሩ።
ክልል ከሆነም በኋላ መረጋጋት የራቀው፣ለኢንቨስትመንትና ለእንግዳ የማይመች አድርጎ በአንዳንድ ወገኖች መታሰቡ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ይህንን የተዛባ አስተሳሰብና ትርክት አንዳንድ ፅንፈኛ ሚዲያዎች ሲያራግቡት እንደሚሰማም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ሆኖም አዲሱ የሲዳማ ክልል ከየትኛውም አካባቢ በተሻለ ሁኔታ መረጋጋት የሚታይበትና ሠላማዊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ህዝቡም ተባባሪና አብሮነትን የሚፈልግ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደስታ በተለይ እስካሁን የመጠበት የሰላም መንገድ ከዚህ በኋላም የሚቀጥሉበት አቅጣጫ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
እኛ የፊት መሪዎችም አተያይ አካታችና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት አበክረን የምንሰራ መሆኑን ነው ብለዋል።
በተለይ አካባቢው ያለውን የመልማት እድሉንና አቅሙን በመጠቀም ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ በመከተል ኢንቨስትመንቱ ፈጥኖ እንደሚነቃቃ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በሚመጣው ልማት ሁላችንም ተባብረንና ተሳስረን የምንጠቀምበት መሆኑን ግንዛቤ የመፍጠርና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ይደረጋል ሲሉ አቶ ደስታ ተናግረዋል።
የአመለካከት ግንባታ ብቻውን ውጤት ስለማያመጣ የህግ የበላይነትን ከማስጠበቅ አንፃር የክልሉን የጸጥታ ኃይል በማጠናከር ህግን ለማስከበር እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ማህበረሰቡምይህንን ተረድቶ በህግ ተፈፃሚነት ላይ ተባባሪ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ በቀጣይ የሚከናወን ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ክልሉ ሰላማዊ፣ ዜጎች ያለ ስጋት የሚንቀሳቀሱበት፣ለማልማት የመጣ ባለሀብት መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ የሚጠቀምበት፣ህብረተሰቡም የኢንቨስትመንት አውታሮችን በመጠበቅና በመንከባከብ የሚያበረታታበት ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።